ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከፍ ያለውና ጥራት የተገባው አላህ በደልን በነፍሱ ላይ እርም እንዳደረገና አንዱ አንዱን እንዳይበድል በደልን በፍጡራኑ መካከልም እርም እንዳደረገው መናገሩን አብራሩ። ሁሉም ፍጡራን በአላህ መምራትና መግጠም ካልሆነ በቀር ከእውነተኛው መንገድ የጠመሙ ናቸው። መመራትን ከአላህ የጠየቀ ሰው አላህም ይገጥመዋል ይመራዋልም። ፍጡራን በሁሉም ጉዳዮቻቸው ወደ አላህ ፈላጊዎች ናቸው። አላህን የጠየቀን ሰው አላህም ጉዳዩን ይፈፅምለታል ይበቃዋልም። ፍጡራን ሌት ተቀን ወንጀል ይፈፅማሉ። አላህ ደግሞ ባሪያው ምህረትን በሚጠይቀው ወቅት ይሸሽገዋልም ያልፈዋልም። ፍጡራን አላህን አንዳችም ሊጎዱም ወይም ሊጠቅሙ አይችሉም። ፍጡራን ሁሉ እንደ አንድ አላህን እጅግ የሚፈራ ቀልብ ያለው ግለሰብ ቢሆኑ ፍራቻቸው በአላህ ንግስና ላይ አትጨምርም። ሁሉም እንደ አንድ ጠማማ ቀልብ ያለው ሰውዬ ቢሆኑም ጥመታቸው በንግስናው ላይ አንዳችም አይቀንስም። ምክንያቱም ደካሞችና ወደ አላህ ፈላጊዎች ናቸውና። በሁሉም ሁኔታ፣ ዘመንና ስፍራ ወደርሱ ፈላጊዎች ናቸው። የተብቃቃም እሱ ብቻ ነው። ፍጡራን ሁሉ ሰዉም ጋኔኑም ከመጀመሪያቸው እስከመጨረሻቸው አላህን ለመጠየቅ በአንድ ስፍራ ላይ ቢቆሙና ከነርሱም ለእያንዳንዱ ሁሉ የጠየቀውን ቢሰጥ ይህ መስጠቱ አላህ ዘንድ ካለው አንዳችም አይቀንስም። ልክ እንደ መርፌ ባህር ውስጥ ገብታ ብትወጣ ባህሩ በዚህ አንዳችም እንደማይቀነሰው ማለት ነው። ይህም የሆነው ከተሟላው ሀብቱ አንፃር ነው። ጥራት ተገባው! ጥራት የተገባው አላህ የባሮችን ስራዎች ይጠብቃልም ያስቀምጣልም። ከዚያም እሷኑ የትንሳኤ ቀን ይመነዳቸዋል። የስራውን ምንዳ መልካም ሆኖ ያገኘው ሰው አላህ ትእዛዙን ለመፈፀም ስለገጠመው አላህን ያመስግን። የስራውን ምንዳ ከዚህ ውጪ ሆኖ ያገኘ ሰውም ወደ ክስረት የመራችውን በመጥፎ የምታዘው ነፍሱን እንጂ ሌላን እንዳይወቅስ።