ዑሥማን አሽሸሓምና ፈርቀድ አስሰብኺይ የታላቁ ሶሓቢይ የአቢ በክራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) ልጅ የሆነው ሙስሊም ዘንድ አባቱ ከነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሙስሊሞች መካከል ስለሚኖር የርስበርስ ፈተናና ጦርነት ሰምቶ ሲያወራ ከሰማ እንዲነግራቸው ሊጠይቁት ሄዱ። እርሱም አዎን! ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ፈተና እንደሚኖር ይህ ፈተናም በሚከሰት ጊዜም ይህንን ፈተና ችላ ብሎ የተቀመጠ ወደርሷ ከሚራመድ ይበልጣል። ምክንያቱም ቁጭ ያለው አይሳተፍባትምም ስለርሷም አይመራመርምና። ወደርሷ የሚራመድም ወደርሷ ለመመርመርና ለመሳተፍ ከሚሮጠው የተሻለ መሆኑን ተናገሩ። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በርሱ ዘመን ፈተናዋ የተከሰተችበት ወይም ያጋጠመችው ሰው የሚጠጋበት ስፍራ ካገኘ ወደዛ እንዲሸሽ እንዲህ በማለት ጥቆማ ሰጡ: ለርሱ የምትሰማራ ግመል ያለው ወደ ግመሉ ይጠጋ፤ ለርሱ የምትሰማራ ፍየል ያለው ሰው ወደ ፍየሉ ይጠጋ፤ ለርሱ መሬት፣ እርሻ ያለው ሰው ወደ መሬቱ ይጠጋ። አንድ ሰውዬም እንዲህ አለ: "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እስኪ ንገሩኝ ግመልም፣ ፍየልም፣ መሬትም የሌለው ሰው ወደየት ይጠጋ?" እርሳቸውም "ወደ መሳሪያው ያምራና ይስበረው ያዶምዱመው ከዚያም መሸሽ ከቻለ ነፍሱንና ልጁን ይዞ ይሽሽ።" አሉ። ከዚያም ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሶስት ጊዜ እንዲህ በማለት አላህን ምስክር አደረጉ: "አላህ ሆይ! መልዕክትህን አደረስኩኝን? አላህ ሆይ! መልዕክትህን አደረስኩኝን? አላህ ሆይ! መልዕክትህን አደረስኩኝን?" አንድ ሰውዬም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እስኪ ንገሩኝ ከሁለቱ ቡድኖች ወይም ጭፍራዎች አንዱን እንድቀላቀል ብገደድና አንዱ በሰይፉ ቢመታኝ ወይም ቀስት መጥቶ ቢገድለኝ ወንጀል ይኖርብኛልን?" አላቸው። እርሳቸውም "የራሱና የተገደለው ሰው ወንጀል ወደርሱ ይመለሳል። የትንሳኤ ቀንም ከእሳት ጓዶች ይሆናል።"