አቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ከነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) አሰጋገድ ባህሪ ከፊሉን ተናገሩ። እርሳቸው ወደ ሶላት የቆሙ ጊዜ ተክቢረተል ኢሕራም እንደሚያደርጉ፤ ቀጥለው ወደ ሩኩዕ በሚሸጋገሩ ጊዜ፣ ሱጁድ በሚያደርጉ ጊዜ፣ ከሱጁድ ራሳቸውን በሚያነሱ ጊዜ፣ ሁለተኛውን ሱጁድ በሚወርዱ ጊዜ፣ ከርሱም ራሳቸውን ቀና በሚያደርጉበት ጊዜ፣ ባለሶስት ወይም ባለአራት ረከዓ ሶላት ውስጥ ለመጀመሪያው ተሸሁድ ከተቀመጡ በኋላ ከሁለተኛው ረከዓ ሲነሱም ተክቢራ እንደሚያደርጉ፤ ቀጥለውም ሶላቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሁሉም የሶላቱ ክፍል ይህንን ይፈፅሙ እንደነበር ተናገሩ። ወገባቸውን ከሩኩዕ በሚያነሱ ጊዜም "ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ" ይሉ ነበር። ከዚያም ከቆሙ በኋላ "ረበና ለከል ሐምድ" ይሉ እንደነበርም ተናገሩ። ከዚያም አቡ ሁረይራ ሶላታቸውን ያጠናቀቁ ጊዜ እንዲህ አሉ: ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ! እኔ የአላህ መልዕክተኛን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሶላት በማመሳሰል ከናንተ እጅግ የቀረብኩኝ ነኝ። ይህቺን አለም እስከሚለያዩ ድረስም የአሰጋገዳቸው ባህሪ ይህቺው ነበረች።