ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) መስጂድ ገቡ። ከርሳቸው በኋላም አንድ ሰውዬ በመግባት በፍጥነት ሁለት ረከዓ ሰገደ። ይሁን እንጂ ሲቆምም፣ ሲያጎነብስም፣ ሱጁድ ሲወርድም እርጋታን አልተላበሰም ነበር። ነቢዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሶላቱን ይከታተሉት ነበር። ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በመስጂዱ አንድ ጎን ስር ተቀምጠው ሳለ ወደርሳቸው በመምጣት ሰላምታ አቀረበላቸው። እርሳቸውም ሰላምታውን ከመለሱለት በኋላ እንዲህ አሉት: አንተ አልሰገድክምና ተመለስና ሶላትህን ደግመህ ስገድ። ተመልሶም ቀደም ብሎ እንደሰገደው በፍጥነት ሰገደና ድጋሚ መጥቶ ለነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ሰላምታን አቀረበ። እርሳቸውም እንዲህ አሉት: አንተ አልሰገድክምና ተመልሰህ ስገድ። ይህንንም ሶስት ጊዜ ፈፀመ። ሰውዬውም "በእውነት በላኮት ጌታ እምላለሁ! ከዚህ ውጪ አሳምሬ መስገድ አልችልምና አስተምሩኝ።" አለ። ነቢዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ አሉት: "ወደ ሶላት የቆምክ ጊዜ የመክፈቻ ተክቢራ አድርግ፤ ከዚያም የቁርአን እናትን (ፋቲሓን)ና አላህ እንድትቀራ የሻልህን ቅራ፤ ከዚያም ባጎነበስክበት ሁኔታህ ላይ ሆነህ እስክትረጋጋ ድረስ አጎንብስ። ይህም መዳፎችህን ጉልበቶችህ ላይ በማድረግና ወገብህን በመዘርጋት ለሩኩዕህ በመመቻቸት ነው።፣ ከዚያም ቀና በል፤ አጥንቶችህ ወደ መገጣጠሚያቸው እስኪመለሱና ቆመህ እስክትስተካከል ድረስ ጀርባህን ቀጥ አድርግ፤ ከዚያም ሱጁድ ላይ ባለህበት ሁኔታ እስክትረጋጋ ድረስ ሱጁድ ውረድ። ይህም ግንባርን ከአፍንጫ ጋር፣ ሁለት እጆችን፣ ሁለቱ ጉልበቶችንና የሁለት እግሮች ጣቶችን ጫፍ መሬት ላይ በማመቻቸት በግንባር መደፋት ነው። ከዚያም በሁለቱ ሱጁዶች መካከል ተረጋግተህ እስክትቀመጥ ድረስ ከሱጁድህ መነሳት ነው። ከዚያም በሶላትህ በሁሉም ረከዓዎች ውስጥ ይህንን ፈፅም።"