ኢብኑ መስዑድ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የጉዳይ ጊዜ ኹጥባን እንዳስተማሯቸው ተናገሩ። ይህም እንደጋብቻና የጁመዓ ኹጥባ በመሰሉ ኹጥባዎችና በጉዳዮቻቸው ወቅት ንግግርን ሲጀምሩ የሚባል ነው። ይህቺ ኹጥባ አጠቃላይ የምስጋና አይነቶች አላህ እንደሚገባው፣ አጋር ከሌለው ከርሱ ብቻ እገዛን መፈለግን፣ ወንጀሎችን መሸሸግና ይቅር ማለትን ከርሱ መፈለግን፣ ከነፍስ ክፋትና ከሌሎችም ሁሉ ክፋቶች ወደርሱ መጠጋትንና ሌሎችንም ትላልቅ ሀሳቦችን ሰብስባለች። ቀጥለውም ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መመራት በአላህ እጅ መሆኑን ፤ አላህ የመራውን ሰው አጥማሚ እንደሌለው ያጠመመውንም መሪ እንደሌለው ተናገሩ። ቀጥለውም ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም የሚለውን የተውሒድን የምስክር ቃልና ሙሐመድ የአላህ ባሪያና መልክተኛ ናቸው የሚለውን የመልክተኝነትን ምስክር ቃል ጠቀሱ። ይህንንም ኹጥባ የአላህን ፊት ፈልጎ የአላህን ትእዛዛት በመፈፀምና ክልከላውን በመራቅ አላህን በመፍራት የሚያዝ እንዲሁም ይህንን የፈፀመ ሰውም ምንዳው ስራውና ንግግሩ ይስተካከላል፣ ወንጀሎቹ ይማራሉ፣ ሀጢአቶቹ ይረግፋሉ፣ በዱንያም ያማረ ህይወት ይጎናፀፋል፣ የትንሳኤ ቀንም በጀነት ስኬትን ይቀዳጀል። የሚልን ሀሳብ በጠቀለሉ እነዚህ ሶስት አንቀፆች ቋጩት።