አነስ ቢን ማሊክ -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና-፦ መስጂድ ውስጥ ሰሐቦች ከነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ጋር ተቀምጠው ሳለ ድንገት አንድ ግመል ላይ ያለ ሰውዬ ገባ። ግመሉን ካንበረከከ በኋላም አሰራት። ከዚያም "ማንኛችሁ ነው ሙሐመድ?" በማለት ጠየቃቸው። ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን በሰዎች መሀል ተደግፈው ነበር። "ይህ የተደገፈው ቀይ ሰውዬ ነው።" አልነው። ሰውዬውም ለርሳቸው፦ "የዐብዱል ሙጠሊብ ልጅ ሆይ!" አላቸው። ነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ለርሱ "ሰምቸሀለሁ ጠይቅ እመልስልሀለሁ።" አሉት። ሰውዬውም ለነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን "እኔ እጠይቆታለሁ ስጠይቆት ጠንከር አደርግቦታለሁና ውስጦ በኔ ቅር እንዳይሰኝ።" አላቸው። ማለትም "በኔ እንዳይቆጡ በኔም መጨናነቅ እንዳያገኞት።" እሳቸውም፦ "የምትፈልገውን ጠይቅ" አሉት። እሱም "በእርሶና ከእርሶ በፊት ለነበሩት ጌታ በሆነው እጠይቆታለሁ! አላህ ነውን ወደ ሰዎች የላኮት?" አላቸው። እውነትነቱን ለማፅናት "አዎን በአላህ ይሁንብኝ" አሉት። ሰውዬውም፦ "በአላህ ስም እማፀኖታለሁ! አላህ ነውን በቀንና በምሽት አምስት ሶላቶች እንድንሰግድ ያዘዞት?" አላቸው። (ግዴታ ሶላቶችን) "አዎን በአላህ ይሁንብኝ" አሉት። "በአላህ ስም እማፀኖታለሁ! አላህ ነውን ከአመት ይህንን ወር እንድንፆም ያዘዘህ?" አላቸው። (ማለትም የረመዳንን ወር) "አዎን በአላህ ይሁንብኝ" አሉት። "በአላህ ስም እማፀንሀለሁ! አላህ ነውን ይህንን ምፅዋት ከሀብታሞቻችን ወስደህ ለድሀዎቻችን እንድታከፋፍል ያዘዘህ?" አላቸው። (ዘካ ለማለት ነው።) ነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን "አዎን በአላህ ይሁንብኝ" አሉት። ይህኔ ዺማም ሰለመ። ለነቢዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ህዝቦቹን ወደ ኢስላም እንደሚጣራ ነገራቸው። ቀጥሎ ራሱን ከበኑ ሰዕድ ቢን በክር የሆነ ዺማም ቢን ሠዕለባህ እንደሆነ በመናገር አስተዋወቃቸው።