የአላህ መልክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ከትላልቆቹ የቂያማ ምልክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ፀሀይ ከምስራቅ መውጣቷን ቀይራ ከምዕራብ እንደምትወጣ ተናገሩ። ሰዎች በሚያዩዋት ጊዜም ሁሉም ያምናሉ። በዚህ ጊዜ ግን ለከሀዲ ኢማኑ አይጠቅመውም፣ መልካም ሥራም ሆነ ተውበትም አይጠቅመውም። ቀጥለው ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሰዎች በዕለትተለት ሁኔታቸውና የህይወት ጉዳያቸው ላይ ሳሉ ቂያማ ድንገት እንደምትመጣ ተናገሩ። ሰዓቲቱ ሻጭና ገዢ ልብሶቻቸውን ለመለዋወጥ ዘርግተው ሳይሻሻጡም ሳይጠቀልሉትም ትከሰታለች። ሰዓቲቱ ሰውዬው የታለበ የግመል ወተቱን ይዞ ሳይጠጣው ትከሰታለች። ሰዓቲቱ ሰውዬው ምንጩን እያስተካከለ በጭቃ እያበጀው ምንም ሳይጠጣ ከሱ ትከሰታለች። ሰዓቲቱ ሰውዬው ወደ አፉ ጉርሻውን ሊበላ እንዳነሳው ሳይበላው ትከሰታለች።