ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በቻልነው መጠን መጥፎ ነገርን እንድንለውጥ ( እንድናስወግድ) አዘዋል። መጥፎ ነገር የሚባለውም፥ አላህና መልክተኛው የከለከሏቸው ሁሉም ነገሮች ናቸው። መጥፎ ነገርን ከተመለከተ አቅም ካለው በእጁ የመለወጥ (የማስወግድ)ግዴታ አለበት። ይህን ማድረግ ከተሳነው ደግሞ መጥፎ ነገር ፈፃሚውን በመከልከል፣ ጉዳቱን ለሱ በማብራራት፣ ከዚህ እኩይ ተግባር ፈንታ እሱን ወደ መልካም በመምራት በአንደበቱ ይለውጠው። ይህኛዉ የመለወጥ እርከን ከተሳነውም ይህን መጥፎ ነገር በመጥላት፣ ለመለወጥ አቅም ቢኖረው ኖሮ እንደሚለውጠው በመቁረጥ በቀልቡ ይለውጠው። በቀልብ መለወጥ (መጥላት) መጥፎ ነገርን የመለወጥ እጅግ ደካማው የኢማን እርከን ነው።