የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ኡመታቸውን ከሰባት አጥፊ ወንጀሎች እንዲርቁ አዘዙ። ምን ምን እንደሆኑ በተጠየቁ ጊዜም ተከታዮቹን ዘረዘሩ፡ የመጀመሪያው : በየትኛውም መልኩ ቢሆን ጥራት ለተገባው አላህ ቢጤን በማድረግ፤ ከአምልኮዎች መካከል ማንኛውም የአምልኮ ዘርፍን ከአሏህ ውጭ ላለ አካል በመስጠት አላህ ላይ ማጋራት መሆኑን ገለፁ፤ በሽርክ የጀመሩበት ምክንያትም ከወንጀሎች ሁሉ ትልቁ ወንጀል ስለሆነ ነው። ሁለተኛ ድግምት፡ - እየቋጠሩ፣ እያነበነቡ፣ መድኃኒትና ጭሳጭስ እያደረጉ የሚሸርቡትን የሚጠቁም ገላጭ ቃል ሲሆን - ድግምቱ የተደረገበትን ሞት ወይም ህመም ላይ በመጣል፣ ወይም በባልና ሚስት መካከል መለያየትን በመፍጠር ተፅእኖ የሚያሳድር ነው። ድርጊቱ ሰይጣናዊ ስራም እንደመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በሽርክ እና መጥፎ መናፍስት የሚወዱትን ነገር እያደረጉ ወደነርሱ በመቃረብ የሚከናወን ነው። ሶስተኛ አስተዳደሩ ተግባራዊ በሚያደርገው ሸሪዓዊ ምክንያት ካልሆነ በቀር አሏህ እርም ያደረጋትን ነፍስ መግደል ነው። አራተኛ በመብላትም ይሁን በሌላ መልኩ በመጠቃቀም ወለድን መውሰድ ነው። አምስተኛ ለአቅመ አዳም ሳይደርስ አባቱ በሞተበት ታዳጊ ገንዘብ ላይ ወሰን ማለፍ ነው። ስድስተኛ ከከሀዲያን ጋር ከሚደረገ ፍልሚያ ማፈግፈግ ነው። ሰባተኛ ጥብቅ የሆኑ ጨዋ እንስቶችን መዝለፍ፤ እንደዚሁም ጨዋ ወንዶችን መዝለፍ ነው።