ዐብደላህ ቢን ዘይድ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና ስለ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዉዱእ አደራረግ በተግባራዊ መልኩ ገለፁ። አነስ ያለ ውሃ የያዘ እቃ እንዲያመጣላቸው ጠየቁ። በመጀመሪያ ሁለት መዳፋቸውን በማጠብ ጀመሩ። እቃውን ዘንበል በማድረግ ውሃውን እያፈሰሱ ሁለት እጆቻቸውን ከእቃው ውጪ አድርገው ሶስት ጊዜ አጠቧቸው። ቀጥለውም እጃቸውን እቃ ውስጥ በመክተት ከርሱ ሶስት ጊዜ እየዘገኑ በያንዳንዱ መዝገን ተጉመጠመጡ አፍንጫቸውም ውስጥ ውሃ እየከተቱ አስወጡ። ቀጥሎ ከእቃው በመዝገን ሶስት ጊዜ ፊታቸውን አጠቡ። ቀጥሎ ከእቃው በመዝገን ሁለት እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ሁለት ጊዜ አጠቡ። ቀጥሎ ሁለት እጃቸውን እቃ ውስጥ በመክተት ካረጠቡ በኋላ ጭንቅላታቸውን በሁለት እጆቻቸው አበሱ። ከጭንቅላታቸው ፊትለፊት በመጀመር ወደ ማጅራታቸው እስኪደርስ ድረስ አበሱ። ቀጥሎ ወደ ጀመሩበት ስፍራ እስኪደርስ ድረስ ሁለት እጃቸውን መለሷቸው። ቀጥሎ ሁለት እግሮቻቸውን ከቁርጭምጭሚታቸው ጋር አጠቡ።