ሙስሊሞች በኸይበር አይሁዶች ላይ በማግስቱ ድልን እንደሚጎናፀፉ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለሶሐቦች ነገሯቸው። ይህም እሳቸው ባንዲራ በሚሰጡት ሰው እጅ ነው። ይህም (ባንዲራ) ሰራዊቶች ለምልክትነት የሚይዙት አርማ ነው። ባንዲራው የሚሰጠው ሰው ባህሪም አላህና መልክተኛውን ይወዳል፣ አላህና መልክተኛውም ይወዱታል። ሶሐቦችም ይህንን ትልቅ ክብር በመፈለግ ባንዲራውን ስለሚሰጠው ሰው ማንነት ሲያወጉ ሌሊታቸውን ተጠምደውበት አደሩ። በማግስቱም ሁሉም ይህን ክብር መጎናፀፍን ተስፋ በማድረግ ወደ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሄዱ። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ስለ ዐሊይ ቢን አቢጧሊብ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና ጠየቁ። አይኖቹን እንደታመመ ነገሯቸው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደርሱ ሰው ላኩና ይዘውት መጡ። ከተከበረው ምራቃቸውም በዐሊ አይኖች ላይ ተፉና ዱዓ አደረጉለት። ምንም በሽታ እንዳልያዘው ሰው እስኪመስል ድረስ ከበሽታው ተፈወሰ። ባንዲራውንም ሰጡትና የጠላት ምሽግ እስኪቀርብ ድረስ በእርጋታ እንዲጓዝ አዘዙት። በነርሱ ላይም ወደ እስልምና እንዲገቡ ጥሪ እንዲያቀርብላቸው፤ እስልምናን ከተቀበሉት በነርሱ ላይ ያለባቸውን ግዴታ እንዲነግራቸው አዘዙት። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደ አላህ የመጣራት ትሩፋቱ አንድ ተጣሪ ለአንድ ሰው መመራት ሰበብ ከሆነ ይህ ለርሱ ዐረቦች ዘንድ ውድ ንብረት የሚባለውን ቀይ ግመል ከሚኖረው ወይም ኑሮት ሰደቃ ከሚሰጠው የበለጠ የተሻለ መሆኑን ለዐሊይ ገለፁለት።