ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የትንሳኤ ቀን አላህ ከፍጡራኖች መካከል ከህዝባቸው አንድ ሰው እንደሚመርጥ ተናገሩ ፤ ሊመረመር ይጠራል፤ በሱ ላይም በዱንያ ይሰራቸው የነበሩትን የወንጀል ተግባራት የያዘ ዘጠና ዘጠኝ መዝገብ ይቀርባል ፤ የእያንዳንዱ መዝገብ ርዝመትም ዓይን የሚያየውን ርቀት ያካልላል። ከዚያም የተከበረውና የላቀው አላህ ለዚህ ሰውዬ፦ "በነዚህ መዝገቦች ውስጥ ከተጻፉት አንድም ብትሆን የምታስተባብለው አለህን?" ይለዋል። "ሥራህን ጸሐፊና ተጠባባቂ የሆኑት መላእክቶቼ በድለውሀልን?" ይለዋል ሰውዬውም "ጌታዬ ሆይ በፍፁም!" ይላል። የተከበረውና የላቀው አላህም "ላንተ በዱንያ አስቀድመህ ለሠራሀቸው ወንጀሎች ተቀባይነት የሚያገኝ ምክንያት አለህን?" በመርሳት፣ በመሳሳት ወይ ባለማወቅ ነው ብለህ ምክንያት የምታቀርብበት ይለዋል። ሰውዬውም፦ "ጌታዬ ሆይ በፍፁም ለኔ ምንም ምክንያት የለኝም።" ይላል። የተከበረውና የላቀው አላህም "እንዴታ! እኛ ዘንድ አንድ መልካም ሥራ አለችህ። እነሆ ዛሬ ባንተ ላይ ምንም በደል የለም" ይላል። ነቢዩ እንዲህ አሉ፦ "ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ ባሪያና መልክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ (አሽሀዱ አን ላኢላሃ ኢለላህ ወ አሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉላህ ) የሚል የተፃፈባት አንድ ካርድ ትወጣለች።" የተከበረውና የላቀው አላህ ለዚህ ሰውዬ፦ "ሚዛንህ ላይ ተገኝ!" ይለዋል። ሰውዬውም በመደነቅ "ጌታዬ ሆይ ይህቺ ካርድ ከነዚህ መዝገቦች ጋር (ስትነፃፀር) ምን ትመዝናለች?" ይላል። የተከበረውና የላቀው አላህም፦ "ባንተ ላይ ምንም በደል አይደርስብህም" አለው። ነቢዩ እንዲህ አሉ፦ " መዝገቦቹ በአንድ በኩል ካርዷ በአንድ በኩል ትቀመጣለች። መዝገቦቹ ያሉበት ሚዛን ስትቀል ካርዷ ያለችበት ሚዛን ደግሞ የከበደችና ሚዛን የደፋች ሆነች። በዚህም አላህ ማረው።