ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) አንድ ሙስሊም አላህ ዘንድ የሚመነዳው ከሙስሊሞች ጋር ከሚሰራው የስራ አይነት አንፃር እንደሆነ ገለፁ። ከአንድ አማኝ ላይ ከዱንያ ችግሮች መካከል አንድን ችግርና መከራ ያቀለለ፣ የገላገለ፣ ያስወገደና ያነሳ ሰው አላህም ከትንሳኤ ቀን ችግሮች መካከል አንድን ችግሩን በማቅለል ይመነዳዋል። ለተቸገረ ያቀለለ፣ ያገራ፣ ችግሩንም ያስወገደ አላህም ለርሱ በዱንያም ሆነ በመጪው ዓለም ጉዳዩን ያቀልለታል። የሙስሊምን ነውር - ለምሳሌ ግልፅ መውጣት የማይገባውን ስህተትና ጥፋት እርሱ ላይ አይቶ - የሸሸገለት ሰው አላህ በዱንያም ሆነ በመጪው ዓለም ነውሩን ይሸሽግለታል። አንድ ሰው ወንድሙን ዲናዊም ይሁን ዱንያዊ ጥቅሞቹ ላይ እስካገዘው ድረስ አላህም ባሪያውን በማገዝ ላይ ይሆናል። ማገዝ በዱዓ፣ በአካል፣ በገንዘብና ከዚህም ውጪ ባሉ ነገሮች ይፈፀማል። የአላህን ፊት ፈልጎበት ሸሪዓዊ ዕውቀትን ለማግኘት የተጓዘን ሰው ወደ ጀነት የሚያደርሰውን መንገድ አላህ ያገራለታል። ሰዎች የአላህን መጽሐፍ ሊያነቡና በመካከላቸው ሊማማሩት ዘንድ ከአላህ ቤቶች መካከል አንድ ቤት ውስጥ ከተሰባሰቡ በነርሱ ላይ እርጋታና ስክነት ይሰፍናል፤ የአላህ እዝነትም ይሸፍናቸዋል፤ መላዕክቶች ያካብቧቸዋል፤ አላህ ዘንድ ቅርብ ከሆኑት ጋር ያሞግሳቸዋል (ያወድሳቸዋል)። አላህ ባሪያውን በላይኛው አለም ማውሳቱ ብቻ ከክብር በቂ ነው። ስራው ጎዶሎ የሆነ ሰው የተሟላ ስራ የሰሩ ሰዎች ደረጃ ላይ አይደርስም። ስለዚህ በዘር ልቅናና በወላጆች ደረጃ ተማምኖ መልካም ስራን ማጓደል አይገባም።