ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ሸይጧን ሌሊት ለመስገድ ወይም ፈጅርን ለመስገድ መቆም ከፈለገ ሰው ጋር ያለውን ሁኔታና ግብግብ ነገሩን። አማኝ ለመተኛት የሄደ ጊዜ ሸይጧን ማጅራቱ ላይ ሶስት ቋጠሮ ይቋጥርበታል። አማኙ ነቅቶ አላህን ካወሳና ለሸይጧን ጉትጎታ እጅ ካልሰጠ አንዷ ቋጠሮ ትፈታለች። ዉዱእ ካደረገ ደሞ ሌላኛዋ ቋጠሮ ትፈታለች ቆሞ ከሰገደ ሶስተኛው ቋጠሮ ይፈታል። የሸይጧን ቋጠሮና ማዳከም ከመወገዱ በተጨማሪ አላህ ለአምልኮ ስለገጠመው በመደሰትና አላህ ቃል በገባለት ምንዳና ምህረት በመበሰር ንቁና ነፍሱም የተደሰተች ይሆናል። ያለበለዚያ ግን ነፍሱ የከበደችው፣ ቀልቡ ያዘነና ከመልካምና በጎ ስራ የተሳነፈ ይሆናል። ምክንያቱም እርሱ በሸይጧን ገመድ የታሰረና ወደ አር‐ራሕማን ከመቅረብ የራቀ ስለሆነ ነው።