ዑሥማን ቢን ዐፋን አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና የነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) መስጂዱ መጀመሪያ ከነበረበት ባማረ መልኩ አድሶ መገንባት ፈለጉ። ሰዎችም መስጂዱ በነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዘመን ከነበረበት ሁኔታ ስለሚለወጥ ይህንን የዑሥማን ሀሳብ ጠሉ። የመስጂዱ ግድግዳ በጡብ የተገነባ ሲሆን ጣሪያው በዘንባባ ቅጠል ነበር የተሰራው። ዑሥማን ግን በድንጋይና በጀሶ ነበር መገንባት የፈለጉት። በዚህ ጊዜ ዑሥማን (ረዺየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና ነቢዩን (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) "ለይዩልኝና ይስሙልኝ ሳይሆን የአላህን ውዴታ ፈልጎ መስጂድ የገነባ አላህ በስራው አይነት የበለጠ ምንዳ ይመነዳዋል። ይህም ምንዳ በገነባው ቤት አምሳያ አሏህም ለርሱ ጀነት ውስጥ የሚገነባለት መሆኑ ነው።" ሲሉ መስማታቸውን ነገሯቸው።