ነቢዩ -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ከባልደረቦቻቸው ጋር ተቀምጠው ነበር። ከመካከላቸውም አቡበከርና ዑመር ይገኙ ነበር። ነቢዩም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ተነስተው ሄዱ። ከዚያም ሳይመለሱ ዘገዩባቸው። የመማረክ ወይም ሌላ የጠላት ጉዳት ደርሶባቸው እንዳይሆን ስጋት አደረባቸው። ሶሐቦችም ረዲየሏሁ ዐንሁም - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ደንግጠው ቆሙ። መጀመሪያ የደነገጠውም አቡ ሁረይራ ረዲየሏሁ ዐንሁ - አላህ መልካም ሥራውን ይውደድለትና - ነበር። እርሳቸውን እየፈለገም የአንድ የበኒ ነጃር የሆነ ሰው አትክልት ግቢ ጋር መጣ። ክፍት በር ለማግኘትም አጥሩን ዞረው። በር ግን አላገኘም። ነገር ግን ግድግዳው ላይ ውሃ የሚገባበት ትንሽ ቀዳዳ አገኘና ሰውነቱን ሰብሰብ አድርጎ ወደ ውስጥ ገባ። ነቢዩንም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- አገኛቸው። እርሳቸውም "አንተ አቡ ሁረይራ?" አሉት። እርሱም "አቤት" አለ። እርሳቸውም "ምን ሆነህ ነው?" አሉት። አቡ ሁረይራም "እርሶ በመካከላችን ነበሩ። ከመካከላችን ተነስተው ሄዱና ዘገዩብን። ከኛ ርቀው ባሉበት ጥቃት ደርሶቦት ፈርተን ደነገጥን። መጀመሪያ የደነገጠውም ሰው እኔ ነበርኩኝ። ይህ የአትክልት ግቢ ዘንድ መጣሁ። ቀበሮ ሰውነቱን ሸምቅቆ እንደሚገባውም ሰውነቴን ሸምቅቄ ገባሁ። የተቀሩት እርሶን የሚፈልጉ ሰዎች ከኋላዬ ናቸው።" ነቢዩም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ለእውነተኝነቱ ምልክት የሚሆን ሁለት ጫማቸውን ሰጡትና እንዲህ አሉት: "እነዚህን ጫማዎች ይዘህ ሂድ። ከዚህ ግቢ ውጪ ያገኘኸውን ላኢላሃ ኢለሏህን ብሎና ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ ከልቡ አምኖበት የሚመሰክርን ሰው እርሱ የጀነት እንደሆነ ንገረው።" መጀመሪያ ያገኘውም ዑመርን ነበር። እርሱም "ምንድናቸው እነዚህ ጫማዎች?" አለው። እርሱም "እነዚህ የረሱል -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ጫማዎች ናቸው። እነዚህን ጫማዎች ሰጥተው ላኢላሃ ኢለሏህን ከልቡ አምኖ የሚመሰክር ሆኖ ያገኘሁትን ሰው በጀነት እንዳበስረው ልከውኝ ነው።" አለ። ዑመርም በእጆቹ የአቡ ሁረይራን ደረት መቱትና በመቀመጫው ወደቀ። እንዲህም አለው: "አንተ አቡ ሁረይራ ተመለስ!" እርሱም "ወደ ነቢዩ -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ደንግጬ፣ ፊቴ ተለዋውጦና እንባ ተናንቆኝ ተመለስኩ። ዑመርም ከኋላዬ ተከትሎኝ መጣ።" ነቢዩም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "አንተ አቡ ሁረይራ ምን ሆነህ ነው?" አሉት። እኔም "ዑመርን አገኘሁት። የላኩኝን ጉዳይም ስነግረው ደረቴ ላይ መቶኝ በመቀመጫዬ ወደቅኩ። ተመለስም አለኝ።" አልኳቸው። ነቢዩም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "አንተ ዑመር ሆይ! ለዚህ ተግባርህ ምን አነሳሳህ?!" አሉት። ዑመርም "እናትና አባቴ ለርሶ ፊዳ ይሁኑና የአላህ መልክተኛ ሆይ! አቡ ሁረይራን ላኢላሃ ኢለሏህን ከልቡ አምኖበት የሚመሰክር ሆኖ ያገኘውን ሰው በጀነት እንዲያበስር ልከውታልን?" አለ። እርሳቸውም "አዎ" አሉ። እርሱም "እንዲህ አያድርጉ። ሰዎች ስራ ሳይሰሩ እርሷን በማለታቸው ላይ ብቻ ጥገኛ ይሆናሉ (ይሳነፋሉ) ብዬ እፈራለሁ። ተዉዋቸው ይስሩ።" አለ። ነቢዩም -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "እንዲያ ከሆነ ተዉዋቸው።" አሉ።