ነቢዩ ( የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በዚህ ሐዲሠል ቁድስ ውስጥ አላህ ስለአጋርያንና ከሀዲዎች እነርሱ እንደሚያስተባብሉት፣ በጉድለትና ነውሮች እንደሚገልፁትና ይህም ለነርሱ እንደማይገባ መናገሩን ገለፁ። አላህን ማስተባበላቸውም: አላህ ካልነበሩበት መጀመሪያ የፈጠራቸው ሲሆን ከሞቱ በኋላም ድጋሚ እንደማይመልሳቸው መሞገታቸው ነው። ምንም እንኳ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ስለሆነ መጀመሪያ መፍጠርም ይሁን ወደነበሩበት መመለስ ከአሏህ አንፃር እኩል ቢሆንም መጀመሪያ ካልነበሩበት የፈጠረ አምላክ እነርሱን በመመለስ ላይም ቻይ መሆኑን ነገራቸው። አላህን መስደባቸውም: ለርሱ ልጅ አለው ማለታቸው ነው። በነርሱ ላይም እርሱ አንድ፣ በስሞቹ፣ በባህሪያቱና በድርጊቱ በሁሉም ምሉዕነት ብቸኛ የሆነ፤ ከሁሉም ጉድለትና ነውርም የጠራ፤ ከማንም የማይፈልግ፤ እያንዳንዱ ሁሉ ግን ወደርሱ የሚፈልጉ የሆነ መጠጊያ፤ ለአንድም አካል ወላጅ ያልሆነ፤ ለአንድም አካል ልጅ ያልሆነ፤ ከአምሳያ ወይም ቢጤ አንዳችም የሌለኝ ነኝ። በማለት መለሰላቸው።