መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አላህ መልካሞችና ኃጢዐቶችን እንደወሰነ ከዚያም ለሚፅፉት ሁለት መላእክቶች እንዴት እንደሚፅፉት እንዳብራራ ገለፁ። መልካምን ለመስራት የፈለገ፣ ያሰበና የቆረጠ ሰው ባይሰራትም እንኳ ለሱ አንድ ምንዳ ትፃፍለታለች። ከሰራት ደግሞ በስራዋ አምሳያ ከአስር እስከ ሰባት መቶ እጥፍ ከዚያም አልፎ እስከ ብዙ እጥፍ ድርብ ትባዛለች። ይህ የምንዳ ጭማሪው ቀልቡ ውስጥ ባለው ኢኽላስ፣ በጥቅሙ ወደ ሌሎች ተሻጋሪነትና በመሳሰሉት ልክ ተንተርሶ ነው ። ኃጢዐትን ለመስራት የፈለገ፣ ያሰበና የቆረጠ ከዚያም ለአላህ ብሎ ሳይሰራት የተዋት ሰው ለሱ አንድ ምንዳ ይጻፍለታል። ወደዛች ኃጢዐት የሚያዳርሱ መንስኤዎችን ካለመፈፀም ጋር በሌላ ነገር በመጠመዱ ሳቢያ ከተዋት ምንም ነገር አይፃፍለትም። ኃጢዐቱን መስራት ስለተሳነው ከተወ ደግሞ በሱ ላይ ያለመው ትፃፍበታለች። ከሰራት ደግሞ አንዲት ሀጢዐት ትፃፍበታለች።