ሐኪም ቢን ሒዛም -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላችውና- ነቢዩን - የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና - የዱንያ መጣቀሚያ የምትሆንን ጠየቀና ሰጡት። ድጋሚ ጠየቃቸውና ሰጡት። ከዚያም ነቢዩ - የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና - እንዲህ አሉት: "ሐኪም ሆይ! ይህ ገንዘብ የሚጓጓለትና የሚከጀል ነው። ይህንን ገንዘብ ሳይለምን ነፍሱ እጅግ ሳትጓጓና ችክ ሳይል ያገኘው ሰው ለርሱ ይባረክለታል። ነፍሱን ለሰዎች በማቅረብና በመከጀል ያገኘው ሰው ለርሱ አይባረክለትም። እርሱም እየበላ እንደማይጠግብ ሰው ምሳሌ ነው። ከላይ ያለች ሰጪ እጅ ከታች ካለች ከምትለምን እጅ አላህ ዘንድ የተሻለች ናት።" ሐኪምም እንዲህ አለ: "የአላህ መልክተኛ ሆይ! በእውነት በላከዎ ጌታ እምላለሁ! ዱንያን እስከምለያይ ድረስ (አሁን ከሰጡኝ) ከርሶ ገንዘብ በኋላ የማንንም ገንዘብ ለምኜ አላጎድልም።" አልኩኝ። የአላህ መልክተኛ ምትክ አቡ በክር - አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና - ሐኪምን ስጦታ ሊሰጠው ይጠራው ነበር። አንዳችም ከርሱ አልቀበልም ብሎ እምቢ አለ። ከዚያም የአማኞች መሪ ዑመርም - አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና - ሊሰጠው ጠራው። ከርሱ ከመቀበልም እምቢ አለ። ዑመርም እንዲህ አለ: "እናንተ ሙስሊሞች ሆይ! እኔ ለሐኪም ከከሃዲያን ጋር ምንም ጦርነትና ጂሃድ ሳይደረግ ከተሰበሰበ ከምርኮ ገንዘብ አላህ ድርሻው ያደረገለትን ሐቁን አቀረብኩለት። እርሱ ግን እምቢ አለ።" ሐኪም እስኪሞት ድረስም ከነቢዩ - የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና - ከተቀበለ በኋላ የአንድንም ሰው ገንዘብ በመውሰድ አላጎደለም ነበር።