የአማኞች እናት መይሙና (ረዲየላሁ ዐንሃ) - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ስለነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የጀናባ ትጥበት ሁኔታ ተናገረች። በቅድሚያ የሚታጠቡበትን ውሃ አቀረበችላቸው። በመሸፈኛም ሸፈነችላቸው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የሚከተሉትን ፈፀሙ: በመጀመሪያ: ውኃ በእጃቸው ላይ አፈሰሱ፤ እቃ ውስጥ ከመክተታቸው በፊትም አጠቧቸው። ሁለተኛ: ውኃ ከቀኝ እጃቸው ግራቸው ላይ አፈሰሱና ከጀናባው ቅሪት የተለጣጠፈውን ለማፅዳት ብልታቸውን አጠቡ። ሶስተኛ: በእጃቸው መሬቱን መቱና ጠረጉት። ቀጥለው ከእጃቸው ላይ ቆሻሻውን ለማስወገድ አጠቡት። አራተኛ: ተጉመጠመጡ: ይህም ውሃን አፋቸው ውስጥ በመክተት አንቀሳቀሱና አሽከርክረው ቀጥሎ ተፉት። "ኢስቲንሻቅም" አደረጉ: ይህም ውሃን አፍንጫቸው ውስጥ በትንፋሻቸው ከሳቡ በኋላ ቀጥሎ ውሃውን አስወጡት። አምስተኛ: ፊታቸውንና ክንዳቸውን አጠቡ። ስድስተኛ: ውሃን በጭንቅላታቸው ላይ አንቧቡ። ሰባተኛ: በተቀረው አካላታቸው ላይም ውሃዉን አንቧቡ። ስምንተኛ: ከታጠቡበት ስፍራ ዘወር ብለው በሌላ ስፍራ መጀመሪያ ያልታጠቡትን እግራቸውን አጠቡ። ቀጥሎ የሚያደራርቁበትን ጨርቅ አመጣችላቸው። እርሳቸው ግን ሳይቀበሏት ውሃውን በእጃቸው ከሰውነታቸው ላይ መጥረግና ማራገፍ ጀመሩ።