ለቂጥ ቢን ሰቢራህ -አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላችውና- ከህዝቦቹ ተመርጦ ከሌሎች ጋር ወደ አላህ መልክተኛ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ከተላኩ የበኒ አልሙንተፊቅ ልዑክ ውስጥ እንደነበረ ተናገረ። እንዲህም አለ: በቤታቸው አላገኘናቸውም ነበር። የአማኞች እናትን ዓኢሻን -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና - አገኘን። በስጋና ዱቄት የሚሰራ (ሐሳእ) የሚባል ምግብ እንዲሰራልን አዘዘች። ለኛም ተሰራልን። በጎድጓዳ ሳህንም ተምር መጣልን። ከዚያም የአላህ መልክተኛ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - መጥተው እንዲህ አሉን "የሆነ ምግብ ቀረበላችሁ?" እኛም "አዎ" አልን። ለቂጥ እንዲህ አለ: እኛ ከአላህ መልክተኛ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - ጋር ተቀምጠን ሳለ የነቢዩ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እረኛ ፍየሎቹን ወደ ማደሪያቸው ሊያስገባ እየነዳ አመጣቸው። ከርሱ ጋርም የምትጮህ የፍየል ግልገል ነበረች። እርሳቸውም "አላራባህምን?" አሉት። እርሱም "ሴት ግልገል ናት።" አላቸው። እርሳቸውም "በርሷ ቦታ አንድ የደረሰች ፍየል እረድልና!" አሉት። ቀጥለውም ነቢዩ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና - እንዲህ አሉ: "ለናንተ ብለን ተጨናንቀን የምናርድላችሁ አድርጋችሁ እንዳታስቡ። እኛ መቶ ፍየል አለን። ከመቶ እንዲጨምር ስለማንፈልግ አንድ አዲስ ግልገል ሲወለድልን በርሷ ቦታ አንድ እናርዳለን።" አሉ። ለቂጥም እንዲህ አለ: "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እኔ ምላሷ ላይ ጣጣ ያለባት አስከፊ ምላስ ያላት ሚስት አለችኝ። ከርሷ ጋር ምን ባደርግ ይሻለኛል?" ብዬ ጠየቅኳቸው። እርሳቸውም "እንደዛ ከሆነ ፍታት" አሉኝ። እኔም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እርሷ ከኔ ጋር የቆየ ቁርኝት አላት። ከርሷም ልጆች አሉኝ።" አልኳቸው። እርሳቸውም "ምከራት! ውስጧ መልካምነት ካለ ምክርህን ትቀበልሃለች። ካልተቀበለች የማያቆስል ምት ምታት እንጂ ሚስትህን የባሪያ አመታት እንዳትመታ።" አሉኝ። ለቂጥም ቀጥሎ እንዲህ አላቸው "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ስለ ዉዱእ ንገሩኝ።" አላቸው። እርሳቸውም "ዉዱእህን ስታደርግ ዉዱእን አዳርሰህ አድርግ። ለሁሉም አካላትህ ሐቁን ስጥ። የዉዱእን ግዴታና ሱና ምንም አትተው። በእጅና እግር ጣቶችህ መካከል ከፋፍትና ፈልፍል። ውሃው ወደ ውስጥህ እንዳይገባ ጾመኛ እስካልሆንክ ድረስ አፍንጫህ ውስጥ ውሃ ስትስብ በደንብ አስገባ።" አሉኝ።