ሶሐቢዩ ጀሪር ቢን ዐብደላህ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ዘንድ እንደነበርና እርሳቸውንም ቃልኪዳን እንደተጋባ ተናገረ። ቃል የተጋባውም በተውሒድ (አላህን በብቸኝነት በማምለክ)፣ በቀንና ምሽት አምስት ግዴታ የሆኑትን ሶላቶች ‐ መስፈርቶቿን፣ ማእዘናቶቿን፣ ግዴታዎቿንና ሱናዎቿን በማሟላት ‐ በመስገድ፣ ግዴታ የሆነውን ዘካ በመስጠት ላይ ‐ ዘካ: ግዴታ የሆነ ገንዘባዊ አምልኮ ሲሆን ከሀብታሞች ተወስዶ ለሚገባቸው ድሆችና ለሌሎችም የሚሰጥ ነው፣ ‐ መሪዎችን በመታዘዝ ላይ፣ ለሁሉም ሙስሊም ተቆርቋሪ (ቅን) በመሆን ላይ ‐ ይህም: ለሙስሊም ጥቅም በመጓጓት፣ መልካምን ለርሱ በማድረስ፣ በንግግርም ሆነ በተግባር መጥፎን ነገር ከርሱ በመከላከል ነው።