አነስ ቢን ማሊክ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) የእናቱ ባል በነበረው በአቡ ጦልሓ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - ቤት ውስጥ ለሚመጡ ሰዎች መጠጥ የሚቀዳው እርሱ እንደነበር ተናገረ። የዛን ግዜ አስካሪ መጠጥ የሚያዘጋጁትም "ቡስር" (ቢጫው ያልበሰለ) ተምር እና ከበሰለው ተምር ቀላቅለው ነበር። ድንገት በአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ትእዛዝ "አዋጅ! በርግጥም አስካሪ መጠጥ ክልክል ተደርጓል።" ተብሎ አዋጅ ተነገረ። አቡ ጦልሓም ለኔ እንዲህ አለኝ "ውጣና ድፋው አፍስሰው!" እኔም ወጥቼ ደፋሁት አፈሰስኩት። አስካሪ መጠጡም በመዲና መንገድ መፍሰሱን ቀጠለ። አንዳንድ ሰዎችም እንዲህ አሉ: "አንዳንድ ሶሐቦች አስካሪ መጠጥ ክልክል ከመደረጉ በፊት ሆዳቸው ውስጥ እያለ ተገድለዋል!" አላህም እነርሱን በማስመልከት ይህንን አወረደ: {በእነዚያ ባመኑትና በጎ ስራዎችን በሰሩት ላይ (ከመከልከሉ በፊት) በተመገቡት ነገር ኀጢአት የለባቸውም።… } [አልማኢዳህ: 93] ማለትም: በነዚያ ባመኑት ላይ አስካሪ መጠጥ ክልክል ከመደረጉ በፊት በበሉትና በጠጡት ምክንያት ወንጀል የለባቸውም ማለት ነው።