ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- የሚምለው ሰው ውሸቱን እንደሆነ እያወቀ በመሃላው የሌላን ሰው ገንዘብ ለመውሰድ በአላህ መማልን አስጠነቀቁ። ይህ ሰውም አላህ የተቆጣበት ሆኖ ይገናኛል። አሽዓሥ ቢን ቀይስም ረዲየሏሁ ዐንሁ የዚህን ንግግር ሰበብ ሲገልፅ እንዲህ አለ: ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ይህንን የተናገሩት በኔና በአንድ አይሁድ ሰውዬ መካከል በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ጭቅጭቅ ስለነበረን ነው። ወደ ነቢዩም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ለመፋረድ ሄድን። ለአሽዓሥም እንዲህ አሉት: "የከሰስከው ነገር ላንተ እንዲፈረድ ማስረጃ ማምጣት አለብህ። ይህንን ካልቻልክ የከሰስከው ተከሳሽህ መሃላው ካልያዘው በቀር ላንተ ምንም መብት የለህም።" አሽዓሥም እንዲህ አለ: "የአላህ መልክተኛ ሆይ! እንዲህ ከሆነማ ይህ አይሁድ ሰውዬ ምንም ሳይገደው ምሎ ገንዘቤን ይወስዳል።" አላህም ይህንን ንግግር በቁርአን ለማረጋገጥ ይህንን አወረደ: {እነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን የሚለውጡ} ትእዛዙ አማኞች አደራን እንዲወጡ እያዘዘ ነው። {በመሃሎቻቸውም (የሚለውጡ)} በውሸት በስሙ የሚምሉ {ጥቂትን ዋጋ} የዱንያን ስብርባሪ ለማግኘት {እነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም ምንም ዕድል የላቸውም።} ምንም ዕጣ የላቸውም። {በትንሳኤ ቀንም አላህ አያነጋግራቸውም።} የሚያስደስታቸውንና የሚጠቅማቸውን ንግግር አያናግራቸውም። ይልቁንም ይቆጣባቸዋል። {የትንሳኤ ቀን ወደነርሱ አይመለከትም።} የእዝነትና የበጎነት እይታን አይመለከታቸውም። {አያነፃቸውምም።} በመልካም እያወሳ አያነፃቸውም። ከወንጀልና ከርክሰትም በምህረቱ አያጠራቸውም። {ለነርሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው።} በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው።