የአላህ መልክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሁሉንም ግዴታ ሶላት ካሰላመቱ በኋላ በዚህ ታላቅ ውዳሴ ያወድሱ ነበር። ትርጉሙም: "ላኢላሃ ኢለሏህ" ማለትም ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም። "ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ" ማለትም አላህ በተመላኪነቱ፣ በጌትነቱ፣ በስሞቹና በባህሪያቶቹ ለሱ ተጋሪ የለውም። "ለሁል ሙልክ" ማለትም ገደብ አልባ ሰፊና ጠቅላይ ንግስና የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግስና ለሱ ነው። "ወለሁል ሐምድ" ማለትም ልቅ በሆነ ምሉእነት የሚገለፅ ፣ በደስታም ይሁን በችግር ወቅት በማንኛውም ሁኔታ በውዴታና በልቅና ምሉዕ በመሆኑ የሚመሰገን ነው። "ወሁወ ዐላ ኩሊ ሸይኢን ቀዲር" ማለትም ችሎታው በሁሉም መልኩ የሞላ አንዳችም የማይሳነው ማንኛውም ጉዳይ ለሱ የማያቅተው ነው። "ላ ሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላህ" ማለት በአላህ እገዛ ቢሆን እንጂ ከአንድ ሁኔታ ወደ አንድ ሁኔታ መለወጥ የለም፤ አላህን ከመወንጀል እርሱን ወደማምለክ መለወጥም ሀይልም የለም። እርሱ አጋዥ ነውና፤ መመኪያም በርሱ ላይ ነው። "ላኢላሃ ኢለሏህ ወላነዕቡዱ ኢላ ኢያህ" "ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም። ከርሱ በስተቀርም አናመልክም።" የሚለው የአላህን ተመላኪነትና ሺርክን ውድቅ የማድረግን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። ከርሱ በስተቀርም አምልኮ የሚገባው የለም። "ለሁ አንኒዕመህ ወለሁል ፈድል" (ፀጋ የርሱ ነው። ችሮታም የርሱ ነው።) እርሱ የፀጋዎች ባለቤትና የሚፈጥር ነው። ለፈለገው ባሮቹም የሚቸረው እሱ ነው። "ወለሁ አሥሠናኡል ሐሰን" በሁለመናው፣ በባህሪያቶቹ፣ በድርጊቶቹ፣ በፀጋዎቹ ሁሉ መልካም ውዳሴዎች ለርሱ የተገባ ነው። "ላኢላሃ ኢለሏህ ሙኽሊሲነ ለሁ ዲን" (አምልኮን ለርሱ ያጠራን ስንሆን ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ የለም።) ማለትም በአላህ አምልኮ ያለምንም ይዩልኝና ይስሙልኝ ብቸኛ ያደረግነው ስንሆን ነው የምናመልከው። "ከሀዲያን ቢጠሉ እንኳ" ማለትም ከሀዲያን ቢጠሉ እንኳ አላህን በመነጠልና በማምለክ ላይ እንፀናለን።