ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ሲመሽና ሲነጋ እነዚህን ዱዓዎች ከማድረግ አይተዉም ነበር። (አላሁመ ኢኒ አስአሉከል ዓፊየተ) አላህ ሆይ! ከአለማዊ በሽታዎች፣ መከራዎችና ችግሮች፣ ከዲናዊ ፈተናዎችና ዝንባሌዎች ሰላም መሆንን (ፊድዱንያ ወልአኺረተ) በቅርቡም ሆነ በመጪው አለም እጠይቅሃለሁ። (አልላሁመ ኢኒ አስአሉከል ዐፍው) አላህ ሆይ! ወንጀሎቼን ማበስ፣ ይቅር ማለትህን (ወልዓፊየተ) ከነውር መፅዳትን (ፊዲኒ) በሃይማኖቴ ከሽርክ፣ ከቢድዓና ከወንጀሎች፤ (ወዱንያየ) በዓለማዊ ህይወቴ ደግሞ ከመከራዎች፣ ከሚያውክና ከክፋቶች (ወአህሊ) በቤተሰቤ ላይ በባለቤቴ፣ በልጆቼና ቅርብ ዘመዶቼ (ወማሊ) በገንዘቤና በስራዬ ላይ ደህና መሆንን እጠይቅሃለሁ። (አልላሁመስቱር ዐውራቲ) አላህ ሆይ! እኔ ላይ ያሉትን ነውሮች፣ ጉድለቶች፣ እንከኖችን ሸሽገኝ፤ ወንጀሌንም አብስ። (ወአሚን ረውዓቲ) ድንጋጤዬንና ፍርሃቴን ደህንነት ስጠው። (አልላሁመሕፈዝኒ) አላህ ሆይ! የሚያውኩኝንና መከራዎችን ከኔ አስወግድልኝ። (ሚን በይኒ የደየ፣ ወሚን ኸልፊ፣ ወዓን የሚኒ፣ ወዓን ሺማሊ፣ ወሚን ፈውቂ) (ከፊት ለፊቴም፣ ከኋላዬም፣ ከቀኜም፣ ከግራዬም፣ ከበላዬም) በዚህም አላህ ከሁሉም አቅጣጫዎች እንዲጠብቃቸው ጠየቁ። መከራዎችና መአቶች ወደ ሰው የሚመጡትና የሚዞሩት ከነዚህ አቅጣጫዎች መካከል በአንዱ ነውና። (ወአዑዙ ቢዐዞመቲከ አንኡግታል) በድንገት ከመያዝና ተዘናግቼ ከምጠፋ በልቅናህ እጠበቃለሁ። (ሚንተሕቲ) በመሬት መደርመስ ከመጥፋትም ባንተ እጠበቃለሁ።