ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አንድ ሙስሊም ወይም ሙእሚን ዉዱእ ያደረገ ጊዜ በዉዱእ ሂደት ፊቱን ሲታጠብ በአይኖቹ የተመለከታቸው ትናንሽ ወንጀሎች ሁሉ ከታጠበ በኋላ ከሚወርደው ውሃ ጋር ወይም ከመጨረሻው የውሃ ጠብታ ጋር ከፊቱ እንደሚራገፍ ገለፁ። እጆቹን የታጠበ ጊዜ ደግሞ እጆቹ የሰራቻቸው ሁሉም ትናንሽ ወንጀሎች ከውሃው ጋር ወይም ከመጨረሻው የውሃ ጠብታ ጋር ከእጁ እንደሚራገፍ ገለፁ። ሁለቱን እግሮቹ የታጠበ ጊዜ ደግሞ እግሮቹ የተራመደችባቸው ሁሉም ትናንሽ ወንጀሎች ከውሃው ጋር ወይም ከመጨረሻው የውሃ ጠብታ ጋር ከእግሩ እንደሚራገፍ ገለፁ። ይህም ውዱኡን ሲያጠናቅቅ ከትናንሽ ወንጀሎቹ ፀድቶ እስኪወጣ ድረስ ነው።