ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) አንድ ሰጋጅ ሶላቱ ውስጥ የተጠራጠረ ጊዜና ሶስት ይሁን አራት ስንት እንደሰገደ ካላወቀ ምን ማድረግ እንዳለበት ገለፁ። ሶስተኛው ስለሆነ የተረጋገጠው አጠራጣሪውን የረከዓ ብዛት (አራትን) ሳይቆጥር አራተኛውን ረከዓ ይሰግዳል። ከዚያም ከማሰላመቱ በፊት ሁለት ሱጁዶችን ይወርዳል። የሰገደው እውነትም አራት ከነበር አንድ ረከዓ በመጨመሩ አምስተኛ ይሆናል። ሁለቱ የመርሳት ሱጁዶችም እንደ አንድ ረከዓ ይሆኑለትና ስለዚህ የረከዓው ብዛት ሙሉ እንጂ ጎዶሎ አይሆንም። ጭማሪዋ ረከዓ እውነትም አራተኛ ከሆነች ደግሞ በርሱ ላይ ያለበትን ግዴታ ሳይጨምርና ሳይቀንስ ተወጥቷል። ሁለቱ ሱጁዶችም ሰይጣንን ማዋረጃና ማራቂያ እንዲሁም ፍላጎቱን ሳያሳካ ባዶ እጁን መመለሻ ይሆናሉ። ምክንያቱም ሶላቱ ውስጥ አወሳስቦበት እንዲበላሽበት ተጋረጠበት፤ ሰጋጁ የአደም ልጅም ‐ ለአደም ሱጁድ ውረድ የሚለውን የአላህን ትእዛዝ ባለመፈፀም ኢብሊስ ያመፀበት የሆነውን ‐ የሱጁድን ትእዛዝ በመፈፀሙ ሶላቱ ሞላለት።