ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- አላህ ባሮቹ ላይ ሶስት ነገሮችን እንደሚወድና በነርሱ ላይም ሶስት ነገር እንደሚጠላባቸው ተናገሩ። በነርሱ ላይ የሚወደው: እርሱን በአምልኮ መነጠላቸው፤ በርሱ ላይ አንዳችንም አለማጋራታቸው፤ በአላህ ቃልኪዳን፣ በቁርአንና በነቢዩ ሱና አንድ ላይ መተሳሰራቸውንና ከሙስሊሙ ህብረት አለመለያየታቸውን ነው። በነርሱ ላይ የሚጠላውም: የማይጠቅማቸውን ትርፍና ዛዛታ ንግግር መናገራቸውን፤ ስላልተከሰተ ነገር መጠየቅ ወይም ሰዎችን ገንዘብ እንዲሰጧቸው፣ በእጃቸው የያዙትን እንዲሰጧቸውና ያላስፈለጋቸውን ነገር መጠየቅ፤ ገንዘብን ማጥፋት፣ ከሸሪዓዊ አላማው ውጪ ለሆነ ጉዳይ ማዋልና ለጥፋት መዳረግ ናቸው።