ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ጀነት ውስጥ የጀነት ሰዎች የሚሰባሰቡበትና መሸጥና መግዛት ሳይጠበቅባቸው የፈለጉትን ነገር የሚወስዱበት ቦታ እንዳለ ተናገሩ። ወደዚህም ስፍራ በየሳምንቱ ይመጣሉ። በሰሜን አቅጣጫ ንፋስ ትነፍስና ፊታቸውንና ልብሳቸውን ታንቀሳቅሳለች። በዚህም ውበትና ቁንጅና ይጨምራሉ። ውበትና ቁንጅና ጨምረውም ወደ ሚስቶቻቸው ይመለሳሉ። ሚስቶቻቸውም ለነርሱ እንዲህ ይሏቸዋል: "በአላህ እንምላለን! ከኛ ከተለያችሁ በኋላ ውበትና ቁንጅና ጨምራችኋል።" እነርሱም ለሚስቶቻቸው እንዲህ ይሏቸዋል: "በአላህ እንምላለን! እናንተም ከተለያየን በኋላ ውበትና ቁንጅና ጨምራችኋል።"