የአማኞች መሪ ዑመር ቢን ኸጧብ ረዺየሏሁ ዐንሁ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - ከተወሰኑ ሶሓቦች ጋር ተቀምጦ ሳለ ለነርሱ እንዲህ አሏቸው: "የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ስለ ፈተና ሲያወሱ የሰማ ማንኛችሁ ነው?" አንዳንዶቹም "እኛ ስለፈተና ሲያወሱ ሰምተናቸዋል።" አሉ። ዑመርም ረዲየሏሁ ዐንሁ "ምንአልባት የሰማችሁት ሰውዬው በግል ህይወቱ ዙሪያ በሚስቱና በልጆቹ ላይ ባለው ወሰን ያለፈ ውዴታው፤ ለነርሱ ባለው ስስት፣ ብዙ መልካም ነገር ትቶ በነርሱ በመጠመድ ወይም ለነርሱ ማሟላት ያለበትን ሐቅ ባለማሟላት፤ ስርዓት ከማስያዝና ከማስተማር ቸልተኛ በመሆን የሚፈተነውን ፈተናና ልክ እንደዚሁ ሰውዬው በጎረቤቱና በመሳሰሉት የሚፈተነውን ፈተና ነው። ይህንን ነው አይደል ሰምተናል ያላችሁት?" አላቸው። እነርሱም "አዎ" አሉ። ዑመርም "ይህ ፈተናማ የሚያስፈርደው አላህን መተሳሰብ ነው። ከነዚህ መካከል እንደሶላት፣ ፆምና ሶደቃ ባሉ መልካም ስራዎችም ሊማሩ የሚችሉ ወንጀሎች አሉ።" አለ። "ነገር ግን ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- አጠቃላይ ስለሆነው፣ ግዝፈቱ ከፍተኛ ስለሆነና ስርጭቱ በብዛት ስለሚዳረስ ባህር እንደሚናወጠው ሰዎችን ስለሚያናውጠው ፈተና ሲያወሩ ማንኛችሁ ነው የሰማው?" አለ። ሰዎችም ዝም አሉ። ሑዘይፋህ ቢን የማንም ረዲየሏሁ ዐንሁ "እኔ ሰምቻለሁ።" አለ። ዑመርም ረዲየሏሁ ዐንሁ ተደሰተ። ለርሱም "አላህ አባትህ ምን አይነት ልጅ እንዲወልድ ነው ያደረገልን! እስኪ ንገረን።" አለው። ሐዘይፋም እንዲህ አለ "ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- እንዲህ ብለዋል: "የተኛ ሰው ጎን ላይ የሰሌን ምንጣፍ እንደሚለጠፈው ፈተናም በሰው ቀልብ ላይ ትለጠፋለችም ግልፅ ትሆናለችም። ፈተናዋ በቀልብ ላይ ከመለጠፏ የተነሳም ቀልቡ ላይ ምልክት ታወጣበታለች። ይህቺ ፈተናም በተደጋጋሚ ተመላልሳ ትከሰታለች። ይህቺ ፈተና የገባችበት፣ የወደዳት፣ መጠጥ ወደ ሰውነት ውስጥ እንደምትቀላቀለው ከቀልቡ ጋር የተቀላቀለችበት ማንኛውም ቀልብ በቀልቡ ላይ ጥቁር ጠብታ ታርፋለች። ይህቺን ፈተና ያልተቀበለ ማንኛውም ቀልብ በቀልቡ ላይ ነጭ ጠብታ ታርፋለች። በዚህም ቀልቦች ሁለት አይነት ይሆናሉ። አንደኛው: በኢማን ላይ ያለው ጥንካሬ ከፍተኛ ስለሆነ፣ ከጉድለት የፀዳ ስለሆነ ፈተናዋ ያልተለጠፈችበትና ምልክት ያላሳረፈችበት ነጭ ቀልብ ነው። የርሱ ቀልብ ምሳሌም ምንም ነገር እንደማይይዝ ለስላሳ አልማዝ ነው። አላህን እስኪገናኝ ድረስም ምንም ነገር አይጎዳውም። ሌላኛው ቀልብ ደግሞ በፈተናው ሰበብ ቀለሙ ወደ ጥቁርነት የተለወጠና ውሃ እንደማይገባበት የተገለበጠ ጆክ የመሰለ ቀልብ ነው። ልክ እንደዚሁ ይህ የጠቆረ ቀልብ መልካምና ጥበብ የማይቀርበው፤ እንዲሁም የወደደውና ለስሜቱ የተመቸው ካልሆነ በቀር መልካሙን መልካም የማይልና መጥፎን የማያወግዝ ቀልብ ነው።" ሑዘይፋም ለዑመር እንዲህ አለው: "ይህ ፈተና አንተ በህይወት እያለህ አይከሰትም። በአንተና በዚህች ፈተና መካከል ሊሰበር የቀረበ የተዘጋ በር አለ።" ዑመርም "ይሰበራልን? ቢከፈትስ ተመልሶ ሊዘጋ ይችላልን?" አለ። ሑዘይፋም "በፍፁም! ይልቁንም ይሰበራል። ይህ በርም የሆነ ሰው መገደሉ ወይም መሞቱ ነው።" አለ። ሑዘይፋ እንዲህም አለ "አሁን ያወራሁት የተረጋገጠ እውነተኛ ወሬ ነው። የፀሃፊዎች ዘገባም የአንድ ሰው የምርምር ሀሳብ ውጤትም አይደለም። ይልቁንም የነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ሐዲሥ ነው።"