ነቢዩ -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ስለበጎ ተግባርና ወንጀል ተናገሩ። እንዲህም አሉ: የበጎ ተግባር ትልቁ ነገር ከአላህ ጋር እርሱን በመፍራት፤ ከፍጡራን ጋር ደግሞ የሚያደርሱብንን አዛ (ችግር) በመቻል፣ ቁጣን በመቀነስ፣ ፊትን በመፍታት፣ ንግግርን በማሳመር፣ ዝምድናን በመቀጠል፣ በመታዘዝ፣ በመራራት፣ በጎ በመስራት፣ መልካም ቤተሰብና ባልደረባ በመሆን መልካም ስነምግባርን መላበስ ነው። በጎ ተግባር ማለት ልብና ነፍስ የረጋበትና የሰከነበት ነገር ነው። ወንጀል ማለት ደግሞ ልብህ ለርሱ ሳይከፈት ነፍስህ ውስጥ የተመላለሰ፣ የከነከነህ አሻሚ ነገር ነው። ስትሰራው ወንጀል ይሆን እያልክ ቀልብህ ውስጥ ጥርጣሬ የሚከሰትበትና የምትፈራው፣ ፀያፍ ስለሆነም አርአያ የሚሆኑ፣ ታላላቅና የተሟላ ስብዕና ያላቸው ሰዎች ፊት ጉዳዩ እንዲታወቅብህ የማትፈልገው ጉዳይህ ነው። ይህም ነፍስ በተፈጥሮዋ ሰዎች መልካም ስራዋን እንዲያውቁላት ነው የምትፈልገው። አንዳንድ ስራዋ ይፋ መውጣቱን ከጠላች ግን ያ ስራ ወንጀል ነውና ምንም መልካም የለውም። በነፍስህ ውስጥ ይህ የብዥታ ምልክት እስካለና በነፍስህ ውስጥ እስከተመላለሰ ድረስ ሰዎች ፈትዋ ቢሰጡህ እንኳ የነርሱን ፈትዋ እንዳትወስድ! ምናልባት ፈትዋ ሰጪው ያለእውቀት ፈትዋ ሰጥቶበት ሊሆን ስለሚችል የጉዳዩ ብዥታነት ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ ፈትዋው ብዥታውን የማስወገድ አቅም የለውም። ነገር ግን ፈትዋው የተሰጠው በትክክል የሸሪዓ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ከሆነ ፈትዋ ጠያቂው ልቡ ለመልሱ ክፍት ባይሆንም እንኳ የግዴታ ወደ ፈትዋው ሃሳብ መመለስ ግዴታ ነው።