ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ስለትላልቅ ወንጀሎች አብራሩ። ትልቅ ወንጀል የሚባለውም ሰሪው በዱንያ ወይም በአኺራ ስለሚቀጣው ቅጣት ከባድ ዛቻ የተዛተበት ነው። የመጀመሪያውም:- "በአላህ ማጋራት ነው።" ይህም ከአምልኮ አይነቶች መካከል ማንኛውንም አምልኮ ከአላህ ውጪ ለሆነ አካል መስጠት ፤ እንዲሁም ከአላህ ውጪ የሆነን አካል በተመላኪነቱ ፣ በጌትነቱ ወይም በስምና ባህሪያቱ አላህ በተለየበት ነገር ላይ ከአላህ ጋር እኩል ማድረግ ማለት ነው። ሁለተኛው:- "የወላጆችን ሐቅ ማጓደል": ይህም ማንኛውም ወላጆችን ወደ ማወክ የሚዳርግ ንግግርም ይሁን ተግባር መፈፀምና ለነርሱ በጎ ማድረግን መተው ማለት ነው። ሶስተኛው: "ነፍስን ያለ አግባብ ማጥፋት ነው።" ይህም በግፍ ወይም ወሰን በማለፍ መግደል ማለት ነው። አራተኛው: "(የሚን አልገሙስ) አስማጭ መሀላ ነው።" ይህም እየዋሸ እንደሆነ እያወቀ በውሸት መማል ነው። በዚህም ስያሜ የተጠራበት ምክንያት ሰውየውን ወንጀል ውስጥ ወይም እሳት ውስጥ ስለምታሰምጠው ነው።