ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለነገሮች ሁሉ የሚያገለግል አጠቃላይ መርህን እያብራሩ ነው። ነገሮች ሁሉ በሸሪዐ መሰረት ወደ ሶስት ክፍሎች ይከፈላሉ: ግልፅ ሐላል ፣ ግልፅ ሐራምና ከፍቁድነትና ክልክልነት አንፃር ብዙ ሰው ብይናቸውን የማያውቃቸው ግልፅ ያልሆኑ አሻሚ ጉዳዮች ናቸው። በሱ ላይ አሻሚ የሆኑበትን ጉዳዮች የተወ ሰው ሀራም ላይ ከመውደቅ በመራቁ ሳቢያ እምነቱ ሰላም ይሆናል፤ ይህን አሻሚ የሆነ ጉዳይ በመፈፀሙ ሳቢያ እሱ ላይ የሚደርስን የሰዎች ትችት ስለማይኖርም ክብሩ ከትችት ሰላም ይሆናል። አሻሚ ጉዳዮችን ያልራቀ ሰው ግን ወይ ሐራም ላይ በመውደቅ ወይ በሰዎች ክብሩ በመዘለፉ ሳቢያ ነፍሱን (ለችግር) ያጋልጣታል። መልክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አሻሚ ጉዳዮች የሚፈፅምን ሰው ሁኔታ ለማብራራት ምሳሌ ጠቀሱ። እሱም ልክ ባለቤቱ በከለላት ስፍራ አስጠግቶ ከብቶቹን እንደሚያሰማራ እረኛ ነው። ቀስ በቀስ የእረኛው ከብቶች ወደተከለለው ስፍራ ቅርብ ስለሆኑ ክልሉ ውስጥ ዘልቀው ሊበሉ ይቀርባሉ። ልክ እንደዚሁ አሻሚ የሆኑ ጉዳዮችን የሚሰራ ሰው በዚህ መዳፈሩ ሳቢያ ወደ ሐራም ይቃረባል። ቀስበቀስ ሐራም ውስጥ ሊወድቅም ይቀርባል። ቀጥለውም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰውነት ውስጥ የምትገኝ ቁራጭ ስጋ እንዳለች ገለፁ። (እሷም ልብ ናት።) በሷ መስተካከል ሰውነት ይስተካከላል በሷ መበላሸትም ሰውነት ይበላሻል።