የአማኞች እናት ዓኢሻ ረዺየሏሁ ዐንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - እንዲህ በማለት ስለ ወሕይ አጀማመር ተናገረች: "የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- መጀመሪያ ወሕይ ወደርሳቸው መውረድ የጀመረው በእንቅልፋቸው መልካም ህልም በማየት ነበር። በእንቅልፋቸው አንድም ህልም አያዩም ነበር እንደ ንጋት ብርሃን በሚመስል መልኩ በግልፅ የሚከሰት ቢሆን እንጂ። ቀጥሎ እርሳቸው ዘንድ ከሰዎች መገለል ተወዳጅ ሆነ። በሒራ ዋሻም ከሰዎች ተገልለው ወደ ቤተሰባቸው ሳይመለሱ በርካታ ቀናቶችን አላህን ሲያመልኩ ያሳልፉ ነበር። ለዚህም ስንቅ ይዘው ነበር የሚወጡት። ቀጥለው ወደ አማኞች እናት ኸዲጃ ረዲየሏሁ ዓንሃ -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና- በመመለስ ለተመሳሳይ ድርጊት ስንቅ ይዘው ይወጡ ነበር። ይህንን ማድረጋቸውንም በሒራ ዋሻ ሳሉ እውነት ወደርሳቸው እስኪመጣ ድረስ ቀጠሉበት። መልአኩ ጂብሪልም ዐለይሂ ሰላም ወደርሳቸው በመምጣት "አንብብ" አላቸው። ነቢዩም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "ማንበብ አልችልም።" አሉ። እንዲህም አሉ: ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝ። ከዚያም ለቀቀኝና "አንብብ" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝ። ከዚያም ለቀቀኝና "አንብብ" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝና እንዲህ አለኝ: {አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም* ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)* አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን} [አልዐለቅ: 1 - 3] ነቢዩም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- አንቀጾቹን ሸምድደው ሞትን ፈርተው ልባቸው እየተንቀጠቀጠ ተመለሱ። የአማኞች እናት ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ ረዲየሏሁ ዓንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ዘንድም በመግባት እንዲህ አሉ: "በልብስ ጠቅልሉኝ! በልብስ ጠቅልሉኝ!" ፍርሃት እስኪለቃቸው ድረስም በልብስ ጠቀለሏቸው። ለኸዲጃም ጉዳዩን ነገሯትና እንዲህ አሉ: "ሞትን በነፍሴ ላይ ፈርቻለሁ።" ኸዲጃም እንዲህ አለች: "ይህንን ከመናገር ተከልከል! በአላህ እምላለሁ! አላህ በፍፁም አይተውህም። አንተ ዝምድናን ትቀጥላለህ፤ ራሱን ያልቻለን ደካማ ታግዛለህ፤ ሰዎች ካንተ ውጪ ማንም ዘንድ በማያገኙት መልኩ በመስጠት ምንም የሌለውን ድሃ ትረዳለህ፤ እንግዳን ታከብራለህ፤ ትክክለኛ ጉዳዮች ላይ ትተባበራለህ።" ኸዲጃም እርሳቸውን ይዛ የአጎቷ ልጅ ወደሆነው ወረቃ ቢን ነውፈል ቢን አሰድ ቢን ዐብዲል ዑዛ ዘንድ ሄደች። በጃሂሊያ ዘመን የጃሂሊዮችን እምነት በመተው ክርስቲያን የሆነ ሰው ነበር። አላህ እንዲፅፍ የሻለትን ያህልም ኢንጂልን በዕብራይስጠኛ ይፅፍ ነበር። አይኑ የታወረ እጅግ የጃጀ ሽማግሌ ነበር። ኸዲጃም ለርሱ እንዲህ አለች: "የአጎቴ ልጅ ሆይ! እስኪ የወንድምህ ልጅ የሚለውን ስማ።" ወረቃም ለርሳቸው "የወንድሜ ልጅ ሆይ! ምንድን ነው የምታየው?" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- የተመለከቱትን ነገሩት። ወረቃም ለርሳቸው "ይህ አላህ በሙሳ ላይ ያወረደው ጂብሪል ነው። ህዝቦችህ ከሀገርህ በሚያስወጡህ ጊዜ ዋ ምኞቴ! ጠንካራ ወጣት በሆንኩ! ዋ ምኞቴ በህይወትም በኖርኩ!" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "እነርሱ ያስወጡኛልን?" አሉ። እርሱም "አዎን አንተ ይዘኸው የመጣኸውን አምሳያ ይዞ የመጣ አንድም ሰው የለም ጠላት ተደርጎ የተያዘና ጉዳት የደረሰበት ቢሆን እንጂ፤ የመልክተኝነት ዘመንህ ላይ ከደረስኩ ጠንካራ እርዳታን እረዳሀለሁ።" አላቸው። ከዚያም ግን ወረቃ ብዙም ሳይቆይ አረፈ። ወሕዩም ለተወሰነ ጊዜ ዘገየ።