ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ሱብሒን ከሰገዱ በኋላ የአማኞች እናት ከሆነችው ከባለቤታቸው ጁወይሪያ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) ዘንድ እርሷ መስገጃ ስፍራዋ ላይ ተቀምጣ ሳለ የንጋቱ መጀመሪያ ላይ ወጡ። ከዚያም ንጋቱ ከተጋመሰ በኋላ በረፋድ ወቅትም ተመለሱ። እርሷም በነበረችበት ቦታ ላይ ከመቀመጥ አልተወገደችም ነበር። እንዲህም አሏት: እስካሁን ስለያይሽ የነበርሽበት ሁኔታ ላይ ከመሆን አልተወገድሽምን? እርሷም "አዎን" አለች። ነቢዩም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ አሉ: ከአንቺ ጋር ከተለያየሁ በኋላ ሶስት ጊዜ ደጋግሜ አራት ንግግሮችን ተናግሬያለሁ። እነዚህ አራት ንግግሮች አንቺ በተቀምጠሽበት ጊዜ ባጠቃላይ ካልሻቸው አዝካሮች ጋር ቢወዳደር ከምንዳ አንፃር እነዚህ አራት ቃላቶች ሚዛን ይደፋሉ። (ሱብሓነሏህ) ከሁሉም ጉድለቶች አላህ ጥራት የተገባው ነው። (ወቢሐምዲሂ) ለዚህ ስለመራንም መልካም ውዳሴ የተገባው ነው። (ዐደደ ኸልቂህ) ቁጥራቸውን ከአላህ በቀር ማንም የማያውቃቸው ፍጡራኑን ያህል (ወሪዷ ነፍሲህ) አላህ ከባሮቹ መካከል ውዳሴውን የወደደለትን ሰው ከርሱ በወደደለት ልክ። ይህም ከርሱ በቀር ማንም የማያካበው ነው። (ወዚነተ ዐርሺህ) ትልቁና ከባዱ ፍጡሩ የሆነው የዐርሽ ክብደት ያህል (ወሚዳደ ከሊማቲህ) የአላህ ንግግር ያህል። የአላህ ንግግር በቁጥር የማይዘለቁና የማያልቁ ናቸው። ይህም ሶስቱንም ክፍሎች ያጠቃልላል። የአላህ ንግግር መጠኑም፣ መገለጫውም፣ ቁጥሩም መጨረሻ የለውም። ነገር ግን በዚህ ንግግራቸው ማለት የፈለጉት ብዛቱን ወሰን የለሽ ለማድረግ ነው። በመጀመሪያ በብዙ ቁጥር ውስጥ የሚካተትን ነገር ገለፁ። እርሱም የፍጡራኑ መጠን ነው። ቀጥለው ከዛም ከፍ ወዳለ አለፉ። እርሱም በነፍሱ ውዴታ መግለፃቸው ነው። ከዚያም ከፍጡራኖቹ ሁሉ በከባድ የሚመዝነው ነው። እርሱም በዐርሽ መግለፃቸው ነው። የመጀመሪያውን ከመጠን አንፃር፣ ሁለተኛው ከሁኔታና ባህሪ አንፃር ሶስተኛውን ደግሞ ከትልቀትና ክብደት አንፃር ገለፁበት።