ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ችግርና ጭንቀት በርሳቸው ላይ በሚበረታ ወቅት እንዲህ ይሉ ነበር፡ "ላኢላሃ ኢለሏህ" ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም። "ታላቅ በሆነው" ክብሩ፣ በማንነቱ፣ በባህሪውና በድርጊቱ ነገሩ የላቀ፤ "ቻይ" ወንጀለኛን በመቅጣት የማይቸኩል ይልቁንም የሚያዘገይ፤ መቅጣት እየቻለ ይቅር የሚል፤ በሁሉም ነገር ላይም ቻይ የሆነ ነው። "ከታላቁ ዐርሽ ጌታ ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም።" የታላቁ ዐርሽ ፈጣሪ ነው። "የሰማያትና የምድር ጌታ ከሆነው አላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም።" የሰማያትና ምድር ፈጣሪ፤ በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረ፤ ባለቤቱ፣ አስተካካዩና እንደፈለገው የሚያስተናብረው ነው። "የተከበረው ዐርሽ ጌታ" የተከበረውን ዐርሽ የፈጠረ ነው።