ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሁሉም ስራዎች ግምት የሚሰጣቸው በኒያ እንደሆነ አብራሩ። ይህ ብይን በአምልኳዊም ጉዳይ ሆነ ከሰው ጋር ባሉ መስተጋብሮች ሁሉንም ስራዎች የሚያጠቃልል ነው። በስራው የሆነን ጥቅም ያሰበ ሰው ከዛች ጥቅም በስተቀር ሌላ አያገኝም። ምንዳም የለውም። በስራው ወደ አላህ መቃረብን ያሰበ ሰው ደግሞ እንደ መብላትና መጠጣት የመሰሉ ተለምዷዊ ስራ ቢሆንም እንኳ ሰርቶ በስራው ምንዳና አጅርን ያገኛል። ቀጥለውም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስራዎች በውጫዊ ይዘታቸው ሲታዩ ተመሳሳይ ከመሆናቸውም ጋር ኒያ በስራዎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ለማብራራት ምሳሌ ጠቀሱ። በስደቱና ሀገሩን በመተዉ የአላህን ውዴታ ማግኘትን ያሰበ ስደቱ ሸሪዐዊና ተቀባይነት ያለው ስደት ነው። ኒያው እውነተኛ ስለሆነም ይመነዳበታል። በስደቱ ግን እንደ ገንዘብ፣ ክብር፣ ንግድና ሚስት የመሳሰሉ ዓለማዊ ጥቅም የፈለገ ሰው ከስደቱ ይህችን ያሰባትን ጥቅም በስተቀር ሌላ አያገኝም። ከምንዳና አጅርም ምንም እጣ ፈንታ እንደሌለው ገለፁ።