ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደ ሐጅ ወይም ዑምራ ተግባር መግባት ሲፈልጉ ይሉት የነበረው ተልቢያ እንዲህ ብለው ነበር: (ለበይከ አልላሁመ ለበይክ) አላህ ሆይ! ወደ ጠራኸን ተውሒድ፣ ስራን ለአላህ ማጥራት፣ ለሐጅና ለሌሎችም አምልኮዎች ቁርጠኛ የሆነ መቀበልን ደጋግሜ ተቀብያለሁ። (ለበይከ ላ ሸሪከ ለከ ለበይክ) አንተ ብቻ ነህ አምልኮ የሚገባህ፣ በጌትነትህ፣ በተመላኪነትህና በስሞችህና በባህሪያቶችህም አጋር የለህም። (ኢነል ሐምደ) ምስጋናና ውዳሴ ላንተ ነው የሚገባህ። (ወንኒዕመተ) ፀጋም (ለከ) ከአንተ ነው። አንተው ነህ የምትሰጠን። በሁሉም ሁኔታዎች የምታስተናብረው አንተ ነህ። (ወልሙልኩ) ንግስናም ያንተ ነው። (ላሸሪከ ለክ) የሚጋራህ የሌለ ሁሉም ያንተ ብቻ ነው። ኢብኑ ዑመር - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እዚህ ተልቢያ ላይ ይህን ይጨምሩ ነበር፡ (ለበይከ ለበይከ ወሰዕደይክ) ደጋግሜ ጥሪህን እቀበላለሁ፤ አስደስተኝ። (ወልኸይሩ ቢየደይክ) ሁሉም መልካም የሚገኘው በችሮታህ ነው። (ለበይከ ወርረግባኡ ኢለይክ) ልመናና ፍላጎታችንም የምንፈልገው መልካም ነገርም በእጅህ ወደሆንከው ወዳንተ ነው። (ወልዐመሉ) ስራም ለአንተ ነው። አምልኮ የሚገባው ለአንተ ብቻ ነው።