ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ሙስሊሞችን በሰባት ነገሮች አዘዙ፤ ከሰባት ነገሮችም ከለከሏቸው። ያዘዟቸውም ነገሮች: የመጀመሪያው: በሽተኛን መጠየቅ ነው። ሁለተኛው: ጀናዛን መሸኘት፣ በርሱ ላይ መስገድ፣ መቅበርና ለርሱ ዱዓ ማድረግ ነው። ሶስተኛው: ላስነጠሰና አላህን ላመሰገነ ሰው "የርሐሙከሏህ" በማለት ዱዓ እንዲደረግለት ነው። አራተኛው: የማለን ሰው መሃላውን ማጥራትና ማረጋገጥ ነው። ማለትም በአንድ ጉዳይ ቢማልና አንተ መሃላው እውን እንዲሆን ማድረግ ከቻልክ ለመሃላው ማካካሻ ለማውጣት እንዳይገደድ የማለበትን ጉዳይ ፈፅም ማለት ነው። አምስተኛው: የተበደለን ሰው በማገዝ፣ በተቻለ መጠን በርሱ ላይ የሚደርሰውን በደል በመከላከል መርዳት ነው። ስድስተኛው: እንደሰርግ፣ ዐቂቃና ሌሎችም የምግብ ጥሪዎችን ለጠራ ጥሪውን ማክበር ነው። ሰባተኛው: ሰላምታ መስጠትንና ሰላምታን መመለስ ማስፋፋትና ማሰራጨት ነው። የከለከሏቸው ጉዳዮች ደግሞ: የመጀመሪያው: የወርቅ ቀለበት መልበስና በርሱ መዋብ ነው። ሁለተኛው: በብር እቃ መጠጣት ነው። ሶስተኛው: በፈረስና በግመል ኮርቻ ላይ በሚነጠፍ የሐር ፎጣ ላይ መቀመጥ ነው። አራተኛው: (አልቀስሲይ) ከተልባ እግር (ከበፍታ) እና ከሐር ተቀላቅሎ የተሰራን ልብስ መልበስ ነው። አምስተኛው: የሐር ልብስ መልበስ ነው። ስድስተኛው: በወፍራም ሐር የተሰራን ልብስ መልበስ ነው። ሰባተኛው: ዲባጅ መልበስ ነው። እርሱም: ከሐር አይነቶች መካከል ምርጡና ውዱ ነው።