ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ከአማኞች ሰባት አይነት ሰዎችን ከአላህ ጥላ ውጪ ሌላ ጥላ በሌለበት ቀን አላህ ከዐርሹ ጥላ ስር እንደሚያስጠልላቸው አበሰሩ። አንደኛ: ወንጀለኛ ባለመሆን በራሱ ላይ ፍትሃዊ የሆነ፤ የሚመራቸውንም ህዝቦች ባለመበደል በህዝቦቹ መካከል ፍትሃዊ የሆነ መሪ ነው። ይህም ትልቅ ስልጣን የተሸከመ ሰው ነው። በተመሳሳይም የሙስሊሞችን ጉዳይ የሚመራ ፍትሃዊ የሆነ ሰው ሁሉ እዚህ ውስጥ ይካተታል። ሁለተኛ: አላህን በማምለክ ያደገ ወጣት፤ እስኪሞት ድረስም ወጣትነቱንና የንቃት እድሜውን በዚሁ ሁኔታ የጨረሰ ሰው ነው። ሶስተኛ: ቀልቡ ወደ መስጂድ የተንጠለጠለ ሰውዬ ነው። መስጂድን በደንብ ስለሚወድና አብዝቶ መስጂድ ውስጥ ስለሚያሳልፍ ከመስጂድ በወጣ ቁጥር ወደ መስጂድ እስኪመለስ ድረስ ይጓጓል። ከመስጂድ ውጪ ሆኖ አካሉ የሆነ ነገር ቢያጋጥመው እንኳ ቀልቡ መስጂድ ላይ እንደሆነ የሚቀጥል ነው። አራተኛ: በትክክል ለአላህ ብለው የተዋደዱ ሁለት ሰዎች በእምነታዊ ውዴታ ላይ ሆነውም የዘወተሩ፤ በአካል ወይም በርቀት ባይገናኙ እንኳ በመካከላቸው ሞት እስኪለያያቸው ድረስ በአለማዊ ጉዳይ ያልተቆራረጡ ናቸው። አምስተኛ: የጥሩ ዘር፣ የልቅና፣ የክብር፣ የገንዘብ፣ የቁንጅና ባለቤት የሆነች ሴት ከርሷ ጋር ዝሙት እንዲፈፅም ፈልጋው እኔ አላህን እፈራለሁ በማለት እምቢ ያለ ሰውዬ ነው። ስድስተኛ: ቀኙ የምትሰጠውን ግራው እስከማታውቅ ድረስ በመደበቅና ይዩልኝ ውስጥ ሳይገባ ትንሽም ይሁን ብዙ ምፅዋትን የመፀወተ ሰው ነው። ሰባተኛ: ከሰዎች ገለል ብሎ አላህን በቀልቡ በማስታወስ ወይም በምላሱ ዚክር በማለት ያወሳና አላህን በመፍራትና በማላቅ ሁለት አይኖቹ ያነቡ ሰው ነው።