ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የእዝነት መላዕክቶች ውሻና ነፍስ ያላቸው የፍጡራን ስዕል ወዳለበት ቤት እንደማይገቡ ተናገሩ። ይህም ነፍስ ያለበት ምሥል አስከፊ ወንጀል ስለሆነ፤ ከአላህ አፈጣጠር ጋር መፎካከር ስለሆነ፤ የሽርክ መዳረሻም ስለሆነ፤ አንዳንዶቹ ምሥሎችም ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ምሥሎች ስለሆኑ ነው። ውሻ ያለበት ቤት ከመግባት የመቆጠባቸው ምክንያት ደግሞ: በብዛት ነጃሳ ስለሚመገብ፤ አንዳንዶቹም ሸይጧን ተብለው ስለተጠሩ ነው። መላዕክት ደግሞ የሸይጧን ተቃራኒ ናቸው። በተጨማሪ የውሻ ሽታ አፀያፊ ስለሆነ ነው። መላዕክት ደሞ መጥፎ ሽታን ይጠላሉ። ስለዚህ ውሻን ማሳደግ ተከለከለ። የሚያሳድግ ሰውም የእዝነት መላዕክት ቤቱ ባለመግባታቸው፤ ለቤቱ ዱዓእ ባለማድረጋቸው፤ ለርሱ ምህረት ባለመጠየቃቸው፤ ለርሱና ለቤቱ በረከት ባለመጠየቃቸው፤ የሸይጧንን ጉዳት ከርሱ ላይ ባለመከላከላቸው ተቀጣ።