ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቁርአንን በመቅራትና በርሱ ከመጠቀም አንፃር የሰዎችን ክፍል ገለፁ። የመጀመሪያው ክፍል: ቁርአንን የሚቀራና በርሱ የሚጠቀም ሙእሚን ሲሆን እርሱም እንደ ትርንጎ ፍሬ ምሳሌ ነው። ጣዕሙና ሽታው ምርጥ፣ መልኩ ያማረና ጥቅሙም ብዙ ነው። በሚቀራው ቁርአን ይሰራበታልም የአላህን ባሮችም ይጠቅምበታል። ሁለተኛው: ቁርአንን የማይቀራ ሙእሚን ነው። እርሱም እንደ ቴምር ምሳሌ ነው። ጣዕሙ ምርጥ ሲሆን ሽታ ግን የለውም። ቴምር በጣዕሟ ጣፋጭነትን እንደሰበሰበችው የዚህም ሙእሚን ቀልብ ኢማንን ሰብስቧል። ቴምር ሰዎች በግልፅ የሚያሸቱት መአዛ እንደሌለው ሁሉ እርሱም ሰዎች በመስማት የሚረኩበትን አቀራር ግልፅ አያደርግም። ሶስተኛው: ቁርአንን የሚቀራ ሙናፊቅ ነው። እርሱም እንደ አሪቲ ነው። እርሷ ምርጥ ሽታ ቢኖራትም ጣዕሟ ግን መራራ ነው። ቀልቡ በኢማን አልተስተካከለም፣ በቁርአን አይሰራም፣ ሰዎች ፊት ግን አማኝ መስሎ ይቀርባል። የርሷም ሽታ ምርጥ ነው ልክ እንደርሱ አቀራር ይመስላል። ጣዕሟ መራራ ነው ልክ እንደርሱ ክህደት ይመስላል። አራተኛው: ቁርአን የማይቀራ ሙናፊቅ ነው። እርሱም እንደ እንቧይ ነው። ሽታ የላትምም ጣዕሟም መራር ነው። ሽታ የሌላት መሆኗ ቁርአን ስለማይቀራ ሽታ የሌለው ከመሆኑ ጋር ይመሳሰላል። ጣዕሟ መራር መሆኑ በርሱ ክህደት መራርነት ጋር ይመሳሰላል። ውስጡ ከኢማን የተራቆተ ሲሆን ውጫዊ ማንነቱም ጥቅም የሌለው እንደውም ጎጂ ነው።