ነቢዩ -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ሴቶችን አባትም ይሁን ወይም ወንድምም ይሁን ወይም ልጅ ወይም ሌላ ለማንኛውም ለሞተ ሰው ሀዘንን ለመግለፅ ብለው ከሶስት ቀን በላይ መዋብን መተዋቸውን ከለከሉ። መዋብን መተው ሲባል ሽቶ መቀባት፣ ኩል መኳል፣ ማጌጥ፣ ቆንጆ ልብስ መልበስ ማለት ነው። የሞተው ባል ከሆነ ግን አራት ወር ከአስር ቀን መዋብን በመተው ሀዘኗን ትገልፃለች። ለባሏ ሃዘን ስትቀመጥ የ"ዐስብ" ልብስ በቀር ለውበት ተብሎ የተቀለሙን ሁሉ ልብሶች አትለብስም። የዐስብ ልብስ የሚባለው ከስፌት በፊት የሚቀለም የየመን ልብስ ነው። ለውበት ብላ ዓይኗን አትኳልም። ጥሩ መአዛ ያላቸውን ሽቶዎችም ይሁን ሌላ አትቀባም። ነገር ግን ከወር አበባዋ ጨርሳ ስትታጠብ የቀበርቾን ወይም የ"አዝፋር"ን ትንሽዬ ቁራጭ እጣን ቀላቅላ ትታጠባለች። እነዚህ ሁለቱ የታወቁ የእጣን አይነቶች ሲሆኑ ክልከላው ላይ የተጠቀሰው የሽቶዎች መደብ ውስጥ አይካተቱም። ከወር አበባ ለምትታጠብ ሴት የተፈቀደውም ደሙን ተከትሎ የሚመጣውን የብልት መጥፎ ጠረን ለማስወገድ ነው እንጂ ሽቶ ለመቀባት ታልሞ አይደለም።