ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) መካ የተከፈተ እለት ለሰዎች ኹጥባ አደረጉ። እንዲህም አሉ፦ እናንተ ሰዎች ሆይ! አላህ ከናንተ ላይ የድንቁርናን ዘመን ኩራት፣ ትዕቢትንና በአባቶች መኮፈስን አስወግዷል። ሰዎች ሁለት አይነት ብቻ ናቸው። ወይ አማኝ፣ በጎ፣ አላህን ፈሪና ለአላህ ባሪያ የሆነ ነው። ይህ ግለሰብ ሰዎች ዘንድ የተከበረ ዘርና ጎሳ ባለቤት ባይሆን እንኳ አላህ ዘንድ የተከበረ ነው። ወይም ደግሞ ከሀዲ፣ አመፀኛና ጠማማ ነው። ይህም ስልጣንና ክብር ያለው ከተከበረ ዘር እንኳ ቢሆን አላህ ዘንድ ከምንም ነገር ጋር የማይስተካከል የተዋረደና የዘቀጠ ነው። ሰዎች ሁሉ የኣደም ልጆች ናቸው። አላህም ኣደምን ከአፈር ነው የፈጠራቸው። መሰረቱ ከአፈር የሆነ ደግሞ በራሱ ሊኮራና ሊደነቅ አይገባውም። የዚህም ማረጋገጫ እንዲህ የሚለው የአላህ ንግግር ነው፦ {እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ። እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ። አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው። አላህ ግልፅን አዋቂ ውስጥንም አዋቂ ነው።} [ሑጁራት: 13