ሙዓዝ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንዲህ አሉ: ከነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ጋር ጉዞ ላይ ነበርኩ። አንድ እለት እየተጓዝን ሳለ ወደርሳቸው ቀረብ አልኩኝና እንዲህ አልኳቸው: የአላህ መልክተኛ ሆይ! ጀነት የሚያስገባኝና ከእሳትም የሚያርቀኝን ስራ ይንገሩኝ። እርሳቸውም እንዲህ አሉ: በነፍስ ላይ መስራቱ ከባድ ስለሆነ ስራ ነው የጠየቅከኝ። አላህ በርሱ ላይ ላቀለለለት ግን ገርና ቀላል ነው። የእስልምናን ግዴታዎች ፈፅም: የመጀመሪያው: አላህን በብቸኝነት መገዛትና በርሱም አንዳችን አታጋራ፤ ሁለተኛው: በቀንና ምሽት አምስቱን ግዴታ ሶላቶች: ፈጅር፣ ዙህር፣ ዐስር፣ መግሪብና ዒሻን መስፈርታቸውን፣ ማዕዘናቸውንና ግዴታዎቻቸውን አሟልተህ ቀጥ አድርገህ መስገድ ነው፤ ሶስተኛው: ግዴታ የሆነብህን ዘካ ማውጣት ነው: ይህም ገንዘብ በሸሪዓ የተገደበን መጠን በደረሰ ጊዜ ለሚገባው አካል የሚሰጥ በሁሉም ገንዘብ ላይ ግዴታ የሆነ ገንዘባዊ አምልኮ ነው፤ አራተኛው: ረመዳንን ትጾማለህ: እርሱም አምልኮን በመነየት ጎህ ከወጣችበት ወቅት ጀምሮ ፀሐይ እስክትገባ ድረስ ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከሌሎችም የሚያስፈጥሩ ነገሮችም መቆጠብ ነው። አምስተኛው: የሐጅ አምልኮን ለመተግበር አላህን ለማምለክ መካን በማሰብ የአላህን ቤት ሐጅ ማድረግ ነው። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ አሉ: ወደ መልካም በሮች የሚያደርስ መንገድ አላሳውቅህምን? ይህም እነዚህን ግዴታዎችና ሱና ተግባራትን በመከተል ነው: የመጀመሪያው: ሱና ጾም መጾም ነው። ይህም ስሜትን በመስበርና ሀይልን በማድከም ወንጀል ላይ ከመውደቅ የሚከላከል ነው። ሁለተኛው: ሰደቃ (ግዴታ ያልሆነ ምፅዋት) መስጠት ነው። ይህም ወንጀል ከተሰራ በኋላ ወንጀልን ታጠፋለች፣ ታስወግዳታለች፣ ፋናዋንም ታብሳታለች። ሶስተኛው: በሌሊቱ የመጨረሻ ሲሶ የተሀጁድ ሶላት መስገድ ነው። ቀጥለው ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) {ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ} በሶላት፣ በዚክር፣ በመቅራትና በዱዓ {ጌታቸውን ይጠሩታል።} {ለመፍራትና ለመከጀል ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለግሳሉ። ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።} ማለትም የትንሳኤ ቀን በጀነት ውስጥ በሚያገኙት ፀጋ አይኖቻቸው በርሱ የምትረጋበትን ነፍሳቸው አታውቅም። {ይሰሩትም በነበሩት ለመመንዳት።} ቀጥለው ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ አሉ: የሃይማኖቱ መሰረት የሆነውን አልነግርህምን? መሰረቱ በርሱ ላይ የሚደገፍበት ምሰሶውንስ አልነግርህምን? ሻኛውንስ አልነግርህምን? ሙዓዝም (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - "እንዴታ የአላህ መልክተኛ ሆይ!" አለ። ነቢዩም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና: የነገሮች ራስ (ዋና) እስልምና ነው። እርሱም ሁለቱ የምስክር ቃላቶች ናቸው። የሃይማኖቱ መሰረት ከሰውዬው ጋር የሚቆይለት በሁለቱ ቃላት ነው። ምሰሶው: ሶላት ነው። ቤት ያለምሰሶ እንደማይኖር ሁሉ ያለ ሶላትም እስልምና የለም። የሰገደ ሰው ሃይማኖቱ ይጠነክራልም ከፍ ይላልም። ሻኛውና ከፍታው ደሞ በጂሃድና የአላህን ቃል ከፍ ለማድረግ የእስልምና ጠላቶችን ለመዋጋት አቅምን በመለገስ ነው። ቀጥለው ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ አሉ: ቀደም ብዬ የነገርኩህን ነገር የሚያስረውና የሚጠብቀውን ልንገርህን? ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ምላሳቸውን ያዙና "ይህንን ቆጥብ። የማይመለከትህን አትናገር።" አሉት። ሙዓዝም: "ጌታችን በምንናገረው ሁሉ ይቀጣናል? ይተሳሰበናል? ይይዘናልን?" አላቸው። ቀጥለውም ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና "እናትህ ትጣህ" አሉት። በዚህም እርሱን መርገም ፈልገው ሳይሆን ነገር ግን ዐረቦች ሊታወቅና ሊገነዘቡት የሚገባን ነገር ለማስገንዘብ የሚናገሩት ንግግር ነው። ቀጥለው "እንደ ክህደት፣ ዘለፋ፣ ስድብ፣ ሀሜት፣ ነገር ማሳበቅ፣ ቅጥፈትና በመሳሰሉት ምላሳቸው ባጨደችው ክፋት ካልሆነ በቀር ሰዎችን እሳት ውስጥ በፊታቸው የሚጥላቸውና የሚደፋቸው (ሌላ ነገር) አለ እንዴ?" አሉት።