ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ከአላህ ውጪ ከመማል አስጠነቀቁ። አማኝ የሆነ ሰው ከአላህ በቀር በማንም አይምልምና። ከአላህ ውጪ የማለና ለምሳሌ በላት፣ በዑዛ የማለ ሰው (እነዚህ ሁለቱ ከእስልምና በፊት በድንቁርና ዘመን ይመለኩ የነበሩ ጣዖታት ናቸው።) ነፍሱን ለማዳን ከሽርክ ለመፅዳትና ለዛ መሀላው ማካካሻ እንዲሆነው አስከትሎ "ላኢላሃ ኢለሏህ" የማለት ግዴታ እንዳለበት ተናገሩ። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለባልደረባው "ና ቁማር እንጫወት" ያለ ሰው (ቁማር ማለት ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች በመካከላቸው አሸናፊው የሚወስደው ገንዘብ መድበው ለመሸናነፍ መጫወት ነው። ከመካከላቸውም እያንዳንዳቸው ወይ ያተርፋል ወይ ይከፍላል።) የጠራበትን ወንጀል ለማካካስ አንዳች ነገር መመፅወቱ እንደሚወደድለት ተናገሩ።